ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ የታሪክ ገጽ ላይ አዲስ የብርሃን ጭረት እየፈጠረ ያለ ታላቅ ሕዝባዊ ክስተት ነው።
ይህ ሒደት የቀደሙ አለመግባባቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በሠለጠነ መንገድ ለመፍታት የተወጠነ ብቻ ሳይሆን፣ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ልጆችን በሀገራዊ ፍቅር ያገናኘ ታላቅ ድልድይ ነው።
የምክክሩ መድረክ የልዩነት ግድግዳዎችን በማፍረስ፣ የጋራ እሴቶችን እና ሀገራዊ አንድነትን እንደገና የመገንባት ታሪካዊ ኃላፊነትን ተሸክሟል።
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ድምፃቸውን ለማሰማት፣ በአካል ወደ እናት ሀገራቸው በመምጣት በየመድረኮቹ መገኘታቸው ለምክክሩ ልዩ ድምቀት እና ጥንካሬ ሰጥቶታል።
በውጭ ሀገራት ያካበቱትን ዕውቀት፣ ተሞክሮ እና ዓለም አቀፋዊ ዕይታ ከሀገር ውስጥ ማኅበረሰብ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማቀናጀት፣ መፍትሔ አመላካች ሐሳቦችን በነፃነት እያቀረቡ ይገኛሉ።
ይህ የውጭው እና የውስጡ የሐሳብ ውህደት ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሔ የመንደፍ አቅምን በከፍተኛ ደረጃ ያሳድገዋል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ዳያስፖራው ከሀገር ውስጥ ወንድም እና እኅቶቹ ጋር ፊት ለፊት ተቀማምጦ መወያየቱ፣ የቆዩ ስጋቶችን ለመቅረፍ እና እውነተኛ መደማመጥን ለመፍጠር ዕድል ፈጥሯል።
በወንድማማችነት እና በአንድነት ስሜት የሚካሄደው ይህ ውይይት፣ በሀገር ሕልውና ላይ የሚጋረጡ ፈተናዎችን በጋራ ለመመከት የሚያስችል ጠንካራ ማኅበራዊ መሠረት እየጣለ ነው።
ዛሬ የሚዘራው የመደማመጥ እና የመከባበር ዘር፣ ለነገዋ የተረጋጋች ኢትዮጵያ እውነተኛ ፍሬ የሚያፈራ ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የሁሉንም ዜጎች አቅም እና ምኞት በአንድ ጥላ ሥር ያሰባሰበ ታሪካዊ ሒደት ነው።
በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉት ንቁ ተሳትፎ፣ የምክክሩን ውጤት ሙሉ እና አካታች ያደርገዋል።
ይህ በጋራ ጥረት የሚጻፍ አዲስ የሀገራችን ታሪክ፣ ለቀጣዩ ትውልድ የምናስረክባትን የበለጸገች፣ የተከበረች እና የጸናች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሩን የሚከፍት ነው።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: