ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ ግብጽ የውጭ ፖሊሲዋን ዋነኛ ማዕከል ያደረገችው ኢትዮጵያን የባሕር በር አልባ ማድረግ እና የዓባይ ወንዝን በበላይነት መቆጣጠር ላይ ነው።
ለዚህ የረዥም ጊዜ የጥፋት ዓላማዋም ኤርትራን እንደ ዋነኛ መሣሪያ ስትጠቀምባት ኖራለች። የግብጽ ንጉሥ የነበሩት ፋሩቅ ኤርትራ ለግብጽ እንድትሰጥ ወይም ምዕራባዊው የቆላማ ክፍል ከሱዳን ጋር እንዲቀላቀል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላይ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጫና ሲያደርጉ እንደነበር በታሪክ ተመዝግቧል።
ይህ የመከፋፈል እና የመጠቅለል ሤራ ሳይሳካ ሲቀር ካይሮ ስልቷን በመቀየር በ1950ዎቹ መገባደጃ የኤርትራ አማፂያንን ወደ ማደራጀት እና ማስታጠቅ ፊቷን አዞረች።
የኤርትራ ነፃነት ግንባር (ጀብሃ) በካይሮ መመሥረቱ ብቻ ሳይሆን፣ ግብጽ ወታደራዊ ሥልጠና እና የፕሮፓጋንዳ ድጋፍ በመስጠት አማፂያኑን ሀገር እስከማፍረስ ላበቃው ትግል ያበረከተችው አስተዋጽኦ የሴራዋ ማሳያ ነው። በኋላም ሻዕቢያን በማስታጠቅ የማወክ ሤራዋን ቀጥላለች።
በ1983 ዓ.ም ኢሕአዴግ አዲስ አበባን በተቆጣጠረበት ወቅት የተፈጠረው የሽግግር መንግሥት፣ የኢትዮጵያን ታሪካዊ እና ጂኦ-ፖለቲካዊ መብት ያላገናዘበ የፖለቲካ ስህተት በመፈጸም ለኤርትራ መገንጠል ዕውቅና ሰጠ።
የሽግግር መንግሥቱ በወቅቱ በነበረው ሥልጣን በእንደዚህ ዓይነት የውጭ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ሕጋዊ ሥልጣን ያልነበፈው መሆኑ ደግሞ የሤራውን ክፋት የሚገልጽ ነው።
ይህንን የችኮላ የመገንጠል ሂደት በማፋጠን በኩል ደግሞ በወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የነበሩት ግብፃዊው ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
ቡትሮስ ጋሊ የካይሮን የረዥም ጊዜ ፍላጎት በዓለም አቀፉ ተቋም ስም በማስፈጸም፣ ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር የሚያገልለው ሪፈረንደም በችኮላ እንዲካሄድ አድርገዋል።
በጥር ወር 1985 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ይህንን ታሪካዊ ስህተት እና የቡትሮስ ጋሊን ጉብኝት በመቃወም አደባባይ ሲወጡ ደማቸው ቢፈስም፣ ዋና ጸሐፊው የተማሪዎቹን አቤቱታ ቸል በማለት ወደ ኤርትራ በማቅናት የግብጽን ድል አክብረዋል።
በዚህ ኢትዮጵያን የባሕር በር አልባ ባደረገው ሂደት ሀገራችን ጂኦ-ፖለቲካዊ አቅሟን ከማጣቷም በላይ፣ ኢትዮጵያውያን ከአሰብ እና አካባቢው ንብረታቸውን ተነጥቀው በግፍ እንዲፈናቀሉ ሆኗል።
ኤርትራ ሀገር ከሆነች በኋላም የሕዝቧን ኑሮ ከማሻሻል ይልቅ ዕድሜዋን ሙሉ የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎች በማስታጠቅ ለግብጽ የገባችውን የትናንት ውለታ ስትከፍል ኖራለች።
ልዩ ልዩ ታጣቂዎችን በማሰልጠን፣ የፕሮፓጋንዳ ሥራዎችን በመሥራት እና ጎረቤት ሀገራትን በማጋጨት ኢትዮጵያን ማመስን የውጭ ፖሊሲዋ ብቸኛ ግብ አድርጋዋለች።
በአሁኑ ወቅት ይህ የጥፋት ትሥሥር አዲስ መልክ ይዞ ብቅ ብሏል። ግብጽ የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማቆም ሳይሳካላት ሲቀር የባሕር በር ጥያቄዋን ለማደናቀፍ ከኤርትራ እና ከሌሎች አካላት ጋር በጋራ እየሠራች ትገኛለች።
ይህ ጥምረት ኢትዮጵያን በምሥራቅ በኩል ቀጣናዊ ከበባ ውስጥ ለማስገባት ያለመ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ታሪካዊው የአሰብ ባለቤት የሆነው የአፋር ሕዝብ ከፍተኛ የሕልውና ስጋት ውስጥ ወድቋል። ሻዕቢያ አፋሮችን ከአሰብ አካባቢ ለማጥፋት፣ ለማደህየት እና ለማፈናቀል ላለፉት 35 ዓመታት ሳይታክት ሲሠራ ቆይቷል።
በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ቀሪው የአፋር ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ከጥንት ርስቱ ተፈናቅሎ፣ አሰብ የግብጽ ወታደራዊ ማስፈጸሚያ እና ጦር ሠፈር ሊሆን ነው የሚል ጥልቅ ስጋት በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ተፈጥሯል።
ኤርትራ አሰብን ለግብጽ አሳልፋ በመስጠት ለኢትዮጵያ ያላትን ጥላቻ ልትወጣ ትችላለች የሚለው ስጋት፣ የቀጣናውን ሰላም ይበልጥ የሚያደፈርስ እና ታሪካዊ ስህተቶችን የሚያደስስ አደገኛ አካሄድ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: