እየተካሄደ ያለው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሂደት እጅግ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ አስታወቁ፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ ስለ ጉባኤው ሂደት አጠቃላይ ሁኔታ በሰጡት መግለጫ እንዳብራሩት፣ በቅድሚያ ስለ አጠቃላይ የምክክር ሂደቱ እና ሊኖሩ ስለሚገባቸው የምክክር ሥነ-ምግባሮች ላይ ግልጽ አቅጣጫ ከተያዘ በኋላ በአሁን ሰዓት በቀጥታ ወደ ዋናው የምክክር መድረክ ተገብቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት ምክክሩ በየቡድኑ በስፋት እየተካሄደ እንደሚገኝ የገለጹት ፕሮፌሰር መስፍን፣ በአሥር አባላት በተዋቀሩ ቡድኖች ተካሂዶ የተጠናቀረው ሀሳብ ከዛሬ ጀምሮ ለሀምሳ አባላት ላሏቸው ቡድኖች መቅረብ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡
እነዚህ የሀምሳ አባላት ስብስቦችም የቀረበላቸውን ሀሳብ በደንብ ካብላሉ በኋላ ለ250ዎቹ ቡድኖች የሚያቀርቡ ሲሆን፣ ይህ የምክክር ሰንሰለታዊ ሂደትም በተመሳሳይ መልኩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል፡፡
በጉባኤው ጅማሮ ላይ ተሳታፊዎች ምንም ዓይነት ሀሳብ ሳይደብቁ በግልጽ እያወጡ እና በስፋት እየተነጋገሩበት መሆኑን የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፣ በዚህም አጠቃላይ የምክክሩ ሂደት በሚፈለገው መንገድ እና በጥሩ ሁኔታ እየተጓዘ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
አክለውም በዚህ መስተጋብር ውስጥ ውይይቱ በተቀመጠለት አቅጣጫ እንዲጓዝ በማድረግ ረገድ የአመካካሪዎች ሚና እጅግ የጎላ እና ትልቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: