በአረንጓዴ ዐሻራ የተገኙ ስኬቶችን በማስፋት የምግብ ሉዓለዊነትን ለማረጋገጥ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን ለመቀነ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ አስታውቀዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሯ የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ በማጃንግ ዞን አስጀምረዋል፡፡
በየዓመቱ እየተከናወነ የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ በክልሉ የደን ሽፋን እንዲጨምር እንዲሁም የአፈር መሸርሸር አደጋ እንዲቀንስ እና ምርት እና ምርታማነት እንዲሻሻል ማስቻሉን ወ/ሮ አለሚቱ ገልጸዋል፡፡
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር የተተከሉ የፍራፍሬ ችግኞች ለምግብነት መዋል በመጀመራቸው የማኅበረሰቡ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲሻሻል አስተዋፅዖ ማበርከቱንም ጠቁመዋል፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራ ስኬትን ለማስቀጠል በክልሉ ለምግብነት እና ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚውሉ የፍራፍሬ እና የአትክልት ችግኞች በስፋት እየተተከሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ማኅበረሰቡም ችግኞችን በመትከል እና በመንከባከብ የጀመረውን ተሳትፎ በማጠናከር በአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ የተገኙ ስኬቶችን ማስቀጠል ይጠበቅበታል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሯ አሳስበዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ኡሞድ በበኩላቸው በክልሉ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር የተፈጥሮ ሀብቱን በዘላቂነት ማልማት የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
በሚፍታህ አብዱልቃድር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: