ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በቃል ኪዳን ሀገራት አሸናፊነት ሲጠናቀቅና ፋሺስት ጣሊያን ስትሸነፍ የኢትዮጵያ አርበኞችና የእንግሊዝ ጦር ጣሊያንን ከኢትዮጵያ ጠራርገው አስወጡ።
በዚህ ወቅት አፄ ኃይለ ሥላሴ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር በመቀላቀል የሀገራችንን የባሕር በር ለማስመለስ ፈጣን እና ሰፊ የዲፕሎማሲ ዘመቻ ጀመሩ።
የጣሊያን የቀድሞ ቅኝ ግዛቶች ዕጣ ፈንታ የመወሰኑ ኃላፊነት አራቱ ኃያላን ሀገራት ማለትም አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና የሶቭየት ኅብረት እጅ ወድቆ ነበር።
እ.አ.አ ፌብሯሪ 10 ቀን 1947 በፓሪስ ከተማ በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሠረት ጣሊያን በአፍሪካ የነበራትን የቅኝ ግዛት መብት በሙሉ አጣች።
በእነዚህ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ፈረንሳይ የአሰብን የባሕር ዳርቻ ከሙሉ ሉዓላዊነት ጋር ለኢትዮጵያ እንዲሰጥ ስታሳስብ፣ አሜሪካ እና እንግሊዝ ደግሞ የደንከል የባሕር ጠረፍ እና አሰብን ጨምሮ ወደ ኢትዮጵያ እንዲካለል አቋም ወስደው ነበር።
ይህም አራቱ ኃያላን ሀገራት የኢትዮጵያን የባሕር በር መብት በተጨባጭ ማረጋገጣቸውን ያሳያል። በዚህ የድኅረ ጦርነት የዲፕሎማሲ ትንቅንቅ ውስጥ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማስከበር ረገድ ወደር የሌለው ጀብዱ የፈጸሙት ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ ነበሩ።
አክሊሉ በፓሪሱ የሰላም ስምምነት ላይ ኢትዮጵያን የወከሉ ሲሆን፣ የሀገራችን ታሪካዊ መብት ለዓለም በማስረዳት እንቅልፍ አልባ ሌሊቶችን አሳልፈዋል።
"የአክሊሉ ማስታወሻ" እንደሚያስረዳው፣ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር ለማዋሃድ እና ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንድትሆን ያደረጉት እልህ አስጨራሽ ትግል በዲፕሎማሲው መድረክ አንጸባራቂ ገድል ነበር።
ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ውህደቱ በሕዝበ ውሳኔ ቢደረግ የተሻለ መሆኑን ያምኑ የነበረ ቢሆንም፣ በወቅቱ በነበረው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ጫና ምክንያት ሀገራችን ፌዴሬሽኑን ለመቀበል ተገድዳለች።
አክሊሉ ለኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ ልዕልና፣ ታሪክ እና ሕልውና መከበር ሲሉ ፌዴሬሽኑን በረቀቀ የዲፕሎማሲ ጥበብ አስተናግደውታል።
አራቱ ኃያላን ሀገራት በኤርትራ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ በአንድ ዓመት ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ መድረስ ባለመቻላቸው ጉዳዩ ወደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ተመራ።
ጠቅላላ ጉባዔውም በርማ፣ ጓቲማላ፣ ኖርዌይ፣ ፓኪስታን እና ደቡብ አፍሪካን ያቀፈ እና ጉዳዩን የሚያጠና ኮሚሽን አቋቁሞ ወደ ስፍራው ላከ።
ይህ ኮሚሽን የኤርትራን ሁኔታ፣ የምሥራቅ አፍሪካን ሰላም እና በተለይም ኢትዮጵያ በጂኦግራፊ፣ በታሪክ እና በኢኮኖሚ ተመሥርታ የምታነሣው "ተገቢ እና ሕጋዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ" አዎንታዊ ምላሽ እንዲያገኝ በማጥናት ሪፖርት አቀረበ።
የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ በውሳኔ ቁጥር 390 (V) መሠረት የኤርትራ ሕዝብን ፍላጎት እና የኢትዮጵያን ታሪካዊ እና ሕጋዊ የባሕር በር መብት በማረጋገጥ ኤርትራ በኢትዮጵያ ዘውድ ሥር በፌዴሬሽን እንድትቀላቀል ታሪካዊ ውሳኔ አሳለፈ።
ይህ ውሳኔ ኢትዮጵያ የተነጠቀችውን የባሕር ወሰን ዳግም እንድትረከብ እና የምጽዋና የአሰብ ወደቦች ሕጋዊ ባለቤት እንድትሆን አስችሏታል።
ኢትዮጵያ የባሕሩ ባለርስት መሆኗን በጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን በረቀቀ የዲፕሎማሲ ጥበብ ጭምር ለዓለም ያረጋገጠችበት ይህ የድኅረ ጦርነት ድል አሁንም ድረስ የትውልድ አኩሪ ታሪካዊ ቅርስ ሆኖ ይኖራል።
የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ጥያቄ የዘመኑ ትውልድ የፈጠረው ምኞት ሳይሆን፣ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ እና ሕጋዊ መሠረት ያለው ጽኑ እውነት ነው። ያለፉት ዘመናት አሻጥሮች ሀገራችንን ከወሰኗ ቢያርቋትም ዛሬ ላይ ያለው ትውልድ ይህን የታሪክ ግድፈት ለማረም በዓለም ፊት የሞራል ልዕልና አለው።
ጥያቄውም ቢሆን በሕግ፣ በዲፕሎማሲ እና በዓለም አቀፍ መርሆች ላይ የተመሠረተ ነው። ስለዚህም እነ ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ እንዳደረጉት የኢትዮጵያ ዳግም ወደ ቀይ ባሕር የመመለስ ራዕይ ፍትሕን፣ ሰላማዊ ድርድርን እና የጋራ ተጠቃሚነትን መሪ ባደረገ መልኩ በቅርቡ ዕውን መሆኑ የማይቀር ነው።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: