የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እስካሁን ያለውን ሂደት በማስመልከት ዛሬ በሰጠው መግለጫ አጠቃላይ አካሄዱ ውጤታማና አዋጭ መሆኑን አስታውቋል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በመግለጫቸው እንዳሉት፣ በምክክር መድረኩ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ሃይማኖት በሌላው ላይ ጫና እንዳያሳድር እና ሂደቱ ወደ አንድ ወገን እንዳያዘነብል ፍትሃዊ አሠራር እየተከተልን እንገኛለን ብለዋል።
በምክክር ሂደቱ የሀሳብ ማመንጨት ምዕራፍ ከተጠናቀቀ በኋላ ከሕዝብ የተሰበሰቡ ከ2 ሺህ በላይ አጀንዳዎችን የማጠናከር ሥራ ተከናውኗል።
ሌሎች ሀገራት በሁለት ወይም በሦስት አጀንዳዎች ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው እንደሚመካከሩ የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፣ በኢትዮጵያ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰበሰቡት በርካታ አጀንዳዎች ተጠቃልለው እና እርስ በርስ ተወራርሰው ወደ ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ዝቅ ማለታቸውን አስረድተዋል።
በዚህም መሠረት በ10 ቡድኖች የተከፋፈሉት ተሳታፊዎች ላለፉት ሦስት ቀናት ሲመክሩባቸው የቆዩዋቸውን አጀንዳዎች አጠናክረው ዛሬ ለ50 ቡድኖች እያቀረቡ ሲሆን፣ እነዚህ የተጠናከሩ ሀሳቦች በቀጣይም ለ500 ቡድኖች ቀርበው ተጨማሪ ውይይት እንደሚደረግባቸው ተገልጿል።
ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ አንጻር ኢትዮጵያ ለምክክር ሂደቱ ጀማሪ በመሆኗ የተለያዩ ትችቶች እና ተግዳሮቶች ቢያጋጥሙም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በአንድ አዳራሽ ውስጥ ተሰባስበው በትህትና እና በሰለጠነ መንገድ እየተመካከሩ ይገኛሉ።
ኮሚሽኑም የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች በጥንካሬ በመወጣት ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ፕሮፌሰር መስፍን አብራርተዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ መገናኛ ብዙኃን የምክክር ሂደቱን ለሕዝብ በማድረስ እያደረጉት ላለው ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበው፣ መላው ኢትዮጵያውያን በያሉበት ሆነው ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን በሃሳብ፣ በመወያየት እና በጸሎት የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: