Search

የባሕር በር፡- የውጭ ምንዛሬ እና የሎጂስቲክስ አዲስ አድማስ

እሑድ ሐምሌ 19, 2018 46

በዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ የባሕር በር ማግኘት ብቻ ሳይሆን፣ የተሻለ የሎጂስቲክስ ሥርዓት መገንባት የአንድ ሀገርን የውጭ ምንዛሬ አቅም፣ የምርት ውድድር እና የኢኮኖሚ ነፃነት ይወስናል።

ለረጅም ጊዜ የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሕልውና እና የንግድ ነፃነት ዋና ምሰሶ ሆኖ ቆይቷል።

የውጭ ምንዛሬ ማለት አንድ ሀገር ከሌላ ሀገር ጋር የንግድ ልውውጥ ስታደርግ የምትጠቀመው የሌላ ሀገር ገንዘብ ነው።ለዓብነትም ያህል ኢትዮጵያ ቡና፣ አበባ ወይም ሌሎች ምርቶችን ወደ ውጭ ሀገር ስትሸጥ በአብዛኛው የምታገኘው ገቢ በዶላር ወይም በሌላ የውጭ ገንዘብ ሊሆን ይችላል።

በአንፃሩ ሎጂስቲክስ ማለት አንድ ምርት ወይም እቃ ከሚመረትበት ቦታ ጀምሮ እስከ ተጠቃሚው  በትክክል፣ በፍጥነት እና በዝቅተኛ ወጪ የማድረስ ሂደት ነው።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት የንግድ መስመሮችን ማሳጠር፣ የማጓጓዣ ወጪን መቀነስ፣ የውጭ ምንዛሬ ፍሰትን ማሻሻል እና የሀገር ውስጥ ምርቶችን ወደ ዓለም ገበያ በተወዳዳሪ ዋጋ ማድረስ የሚያስችል ስትራቴጂካዊ አቅም ነው።

በአሁኑ የዓለም ኢኮኖሚ ውድድር ውስጥ ሎጂስቲክስ የተደበቀ የኢኮኖሚ ኃይል በመሆኑ አንድ ምርት ከፋብሪካ ወደ ዓለም ገበያ ለመድረስ የሚወስደው ጊዜና ወጪ በሀገር ውስጥ የንግድ አቅም ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ያሳድራል። የተሻለ የባሕር በር አጠቃቀም የእቃ ማጓጓዣ ወጪን በመቀነስ የውጭ ምንዛሬ ጫናን ሊያቀል ይችላል።

ከውጭ ምንዛሬ አንፃር፣ የባሕር በር በርካታ ዕድሎችን የሚከፍት ሲሆን የወጪ ንግድ ምርቶች በተወዳዳሪ ዋጋ ወደ ዓለም ገበያ ሲደርሱ የሚገኘው ገቢ የውጭ ምንዛሬ አቅምን ያሳድጋል። በተመሳሳይ የግብዓት ማስገቢያ ወጪዎች መቀነስ የኢኮኖሚውን ጫና በከፍተኛ ሁኔታ ያለዝበዋል።

ከባሕር በር ጋር የተያያዘው የኢትዮጵያ አቋም የሚመራው በጋራ ተጠቃሚነት ሀሳብ ነው። ይህም የባህር በር የግጭት ምንጭ ሳይሆኑ የንግድ፣ የኢኮኖሚ ትስስር እና የአካባቢው ሀገራት ትብብር መሠረት እንዲሆኑ ያበረታታል።

በመሆኑም ዘመናዊ የባቡር መስመር፣ መንገድ፣ የደረቅ ወደቦች፣ የዲጂታል ሎጂስቲክስ ሥርዓት እና የንግድ ማመቻቸት አንድ ላይ ሲቀናጁ የባሕር በር የኢኮኖሚ ሞተር ይሆናል።

በልዩ እሸቱ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: