አንድ ሀገር እንደ ሀገር ጸንታ የምትቆመውና ታሪኳና ድንበሯ ተከብሮ ለትውልድ የሚሸጋገረው በወረቀት ላይ በሚጻፉ ቃላት ብቻ ሳይሆን፣ በመሬት ላይ በሚከፈል የላቀ መስዋዕትነት ነው።
የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ይህንን እውነት በተግባር ያረጋገጠ፤ በብርድና በሐሩር፣ በቁልቁለትና በዳገት ሳይበገር በደሙና በአጥንቱ የሀገርን ታሪክና ማንነት እየጻፈ ያለ የጽናት ተቋም ነው።
ሰራዊታችን ከሁሉም የኢትዮጵያ ማዕዘናት የተውጣጡ ጀግኖች በቋንቋና በባህል ተለያይተው ሳይሆን "በኢትዮጵያዊነት" የጋራ ቃል ኪዳን የተሳሰሩበት የሕብረ ብሔራዊነት ተምሳሌትና የትውልድ ኩራት ነው።
አባላቱ ከፍለው የሚያልፉት ዋጋ የእያንዳንዳችንን ሕይወት፣ የሀገራችንን ክብርና የትውልዱን መጻኢ ዕድል የሚወስን በመሆኑ፤ ለሠራዊታችን የሚሰጠው እውቅና፣ ክብርና ድጋፍ የሁላችንም አገራዊ ግዴታና ኃላፊነት ነው።
የሰራዊታችን መስዋዕትነት የትላንት ታሪካችን መሠረት፣ የዛሬው ሰላማችን ዋስትና እንዲሁም የነገው ተስፋችን መገንቢያ ነው። ምንም እንኳ ጠላቶቹና አውርቶ አደሮች ክብሩን ለማጉደፍ የሐሰት ትርክቶችን ቢፈበርኩም፣ ከትግል ጉዞው ፈጽሞ ሊገቱት አልቻሉም።
ምክንያቱም ከሕዝብ አብራክ ወጥቶ ለሕዝብ የቆመው የኢትዮጵያ ወታደር፣ ሀገርና ሕዝቡን አብዝቶ የሚወድ፣ ሰውን የሚያስቀድምና "እኛነትን" የተላበሰ ልዕለ ሰብዕና ያለው በመሆኑ ነው።
ሠራዊቱ በማይታጠፍ ቃሉ ተልዕኮውን በሚገባ የሚወጣ ቢሆንም፣ የታነጸበት ሕዝባዊ እሴት ሁልጊዜ ምላጭ ከመሳቡ በፊት እንዲያስብና ገዳዩን እንኳ ለማዳን ዕድል እንዲሰጥ ያዘዋል፤ በታሪኩም በጠላቶቹ ተገፍቶ እንጂ በእብሪት ተነሳስቶ የገባበት ጦርነት የለም።
ከዚህም ባሻገር ሠራዊቱ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂና የወታደራዊ ስልት ታጥቆ የሕዝብን ደኅንነት እያረጋገጠ ይገኛል። በመደመር እሳቤ የጸጥታ ተቋማትን ለማዘመን በተሰራው ሰፊ የሪፎርም ሥራ፤ በልዩ ዘመቻዎች ዕዝ፣ በአየር ኃይል፣ በሜካናይዝድ፣ በኤሌክትሮኒክስ ዋርፌር እና በሳይበር አቅም ግንባታ ለሀገር ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው የሚበቃ ዘመናዊ ሰራዊት መገንባት ተችሏል።
በተለይም በድሮን ቴክኖሎጂ እና በዘመናዊ የጦር ሳይንስ ማንኛውንም የውስጥና የውጭ የጸጥታ ስጋት ገና ከጥንስሱ የማምከን ስትራቴጂያዊ የበላይነትን ተጎናጽፏል።
የአባቶቹን አኩሪ ታሪክ በዘመናዊ የጦር ስልት በማዘመን ሀገርን ከማንኛውም ፈተና የሚጠብቀው ይህ ኃይል፣ የጀግንነት ምሳሌ እና የሉዓላዊነታችን እውነተኛ ጋሻ ነው።
በግንባር ደማቸውንና አጥንታቸውን እየገበሩ እኛ በሰላም እንድንወጣና እንድንገባ ላደረጉልን የሀገር የክብር ዘቦች ሁልጊዜም ላቅ ያለ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: