Search

"ምግብ ከግብርና በላይ ነው"፡- የኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነት ጉዞ እና አዲስ እይታ

እሑድ ሐምሌ 19, 2018 36

ዓለማችን በተወሳሰበ የጂኦፖለቲካዊ ሽግሽግ፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና አሳሳቢ በሆነ የኢኮኖሚ መስተጓጎል ውስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት፣ የምግብ ዋስትና ጉዳይ ከሰብዓዊ እርዳታ ጠባብ ማዕቀፍ ወጥቶ የብሔራዊ ደኅንነት እና የስትራቴጂያዊ ሉዓላዊነት መሠረት እየሆነ መጥቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) “ምግብ ከግብርና በላይ ነው፤ ጤናችንን፣ ኢኮኖሚያችንን፣ አካባቢያችንን እና የወደፊት ህይወታችንን ይቀርጻልበማለት የተናገሩት ሐሳብ ይህንን ወቅታዊ እውነታ በግልጽ ያሳያል።

የንግግራቸው አንደምታ ኢትዮጵያም ሆነች አፍሪካ የምግብ ሥርዓታቸውን ከውጭ ጥገኝነት አላቅቀው በራሳቸው አቅም ላይ እንዲገነቡ ጥሪ የሚያቀርብ ሲሆን፣ ይህንንም ለማሳካት ከልማት እርዳታ ይልቅ ፍትሃዊ የኢንቨስትመንት አጋርነት አስፈላጊ ነው፡፡

ይህ አካሄድ አፍሪካን እንደተመጽዋች ከሚያየው የቆየ ትርክት በማላቀቅ፣ አኅጉሪቱ ዓለምን መመገብ ወደምትችልበት አቅም ለማሸጋገር ያለመ  አዲስ የእይታ ለውጥ ነው።

ባለፉት ስምንት ዓመታት በኢትዮጵያ መንግሥት የጀመራቸው እንደ 'የሌማት ትርፋት' የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እና የአረንጓዴ ዐሻራ የመሳሰሉት ውጥኖች መሬት ላይ ተጨባጭ ውጤቶችን በማስመዝገብ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ መሻሻሎችን አሳይተዋል።

ለአብነትም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የተፈጠረውን የስንዴ አቅርቦት መቆራረጥ ተከትሎ ኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሄክታር መሬቶችን በመስኖ ስንዴ በማልማት ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ግዥ ማስቀረት ወደሚያስችልበት ደረጃ መድረሷ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ለምትፈተን ሀገር ትልቅ ድል ነው።

ከዚህም ባሻገር ባለፉት ዓመታት 48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የተተገበረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተራቆቱ መሬቶችን በማገገም፣ የውሃ ሀብትን በማጎልበት እና የግብርና ሥነ-ምህዳሩን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር በማድረግ ረገድ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂያዊ ስኬት አስመዝግቧል።

በተመሳሳይ የሥነ-ምግብ ደኅንነትን ለማረጋገጥ የተነደፈው 'የሌማት ትርፋት' መርሐ ግብር በወተት፣ ማር፣ እንቁላል እና ስጋ ምርት ላይ ያመጣው ሀገራዊ መነቃቃት፣ የሰቆጣ መግለጫን መነሻ በማድረግ የህጻናትን የመቀጨጭ ችግር (Stunting) ለመቅረፍ ከተያዘው ግብ ጋር ተናቦ የምግብ ሥርዓትን ከጤና እና ከሰው ሀብት ልማት ጋር በጠንካራ መሰረት ያስተሳሰረ ነው።

ይህ ሀገራዊ ጥረት ከዓለም አቀፉ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ሲታይ ግን፣ የራሱ የሆነ የፍትሃዊነት ጥያቄን ያስነሳል። አፍሪካ ለዓለም አቀፉ የካርቦን ልቀት የምታበረክተው አስተዋጽኦ እጅግ ዝቅተኛ  ቢሆንም፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለሚከሰቱ ድርቆች እና ጎርፎች ግንባር ቀደም ተጠቂ ነች።

በመሆኑም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚሰጠው የአየር ንብረት ፋይናንስ (Climate Finance) እንደ በጎ አድራጎት ሳይሆን፣ እንደ መብት እና የጋራ ኅልውና ኢንቨስትመንት መታየት አለበት። ይህ ፋይናንስ 70 በመቶ በላይ አፍሪካን የሚመግቡትን አነስተኛ አርሶ አደሮች የቴክኖሎጂ፣ የሜካናይዜሽን እና የዘመናዊ ግብዓት ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ትራንስፎርሜሽኑን የሚያሳካ ይሆናል። እነዚህን ተስፋ ሰጪ ጅምሮች እና ስኬቶች ወደማይቀለበስ ዘላቂ ውጤት ለማሸጋገር ግን ቁልፍ የሆኑ የፖሊሲ እና የተግባር ክፍተቶችን መሙላት የግድ ይላል።

ከምንም በላይ በግብርናው ዘርፍ የሚደረገው ኢንቨስትመንት ፍሬ እንዲያፈራ በተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ማስፈን ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም መረጋጋት ከሌለ የምርት አቅርቦት ሰንሰለቱ ይቋረጣል፣ አርሶ አደሩም ከማሳው ይፈናቀላል።

በተጨማሪም ከውጭ የሚጠበቀውን ኢንቨስትመንት ከመሳብ ጎን ለጎን የሀገር ውስጥ የግል ዘርፉን በግብርና ማቀነባበር እና በመሠረተ ልማት ዘርፍ ያለውን ተሳትፎ በስፋት ማሳደግ ያስፈልጋል።

የጀመርናቸውን የምግብ ዋስትና ውጥኖችን አጠናክሮ በመቀጠል፣ የግብርና ፖሊሲዎች በሚተገበሩበት ጊዜ መሬት ላይ ካለው የአርሶ አደሩ የዘመናት ባህላዊ እውቀት እና ተጨባጭ ፍላጎት ጋር መጣጣም አለባቸው። የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጉዞ የጠንካራ ፖሊሲ፣ የሰላም፣ የታታሪነት እና የዓለም አቀፍ አጋርነት ውኅደትን አጥብቆ የሚሻ የኅልውና ጉዳይ ነው፡፡

በበረከት ሽመልስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: