ቀይ ባሕር… ይህ ስም ለብዙዎች የዓለም አቀፍ ንግድ መስመር፣ የጂኦ-ፖለቲካ ማዕከል እና የኢኮኖሚ ሕልውና ምልክት ነው።
በኢትዮጵያ የስፖርት ታሪክ ማኅደር ውስጥ ደግሞ ስሙ ሲነሣ፤ በደጋፊዎች በተሞሉ ስታዲየሞች፣ በማይረሱ ፍልሚያዎች እና በሕዝቦች የጋራ ወርቃማ ዘመን ይታወሳል።
ዛሬ ኢትዮጵያ የባሕር በር ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ እና በቀጣናዊ ትብብር ዙሪያ ሰፊ ውይይት እያካሄደች ባለችበት ወቅት፣ የቀይ ባሕር እግር ኳስ ክለብ የተወው ታሪካዊ ዐሻራ ሕዝባዊ ትሥሥርን የሚያስታውስ ማሳያ ሆኖ ብቅ ይላል።
ትናንት በአንድ ሀገር ጥላ ሥር በነበረው ጂኦግራፊያዊ አስተዳደር የተፈጠረው ማኅበራዊ እና ስፖርታዊ ትሥሥር በታሪክ መዝገብ ላይ ደማቅ ዐሻራ አኑሯል።
በቀይ ባሕር ጠረፍ ተመሥርቶ በኢትዮጵያ ሊግ ውስጥ እንደ ማዕበል ብቅ ያለው 'ቀይ ባሕር እግር ኳስ ክለብ'፣ በወቅቱ በሀገራችን ብሔራዊ ሊግ ውስጥ ከነበሩ ኃያላን ክለቦች አንዱ ነበር።
የስሙ መጠሪያ ከስትራቴጂያዊው የባሕር ወሰን ጋር መያያዙ ብቻ ሳይሆን በስታዲየሞች ያሳየው የላቀ ብቃት ልዩ ክብር አጎናጽፎታል።
ከቴሌ፣ ከሐማሴን፣ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ከመብራት ኃይል እና ከመቻል ጋር የሚደረጉት ፍልሚያዎች የኢትዮጵያ እግር ኳስ ማሳያዎች እና ሕዝብ ለሕዝብ የሚያቀራርቡ ጠንካራ መድረኮች ነበሩ።
በ1954 ዓ.ም ኢትዮጵያ ብቸኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ስታነሣ፣ የቫሳሎ ወንድማማቾችን ጨምሮ ከቀይ ባሕሩ ጠረፍ አካባቢዎች የተገኙ እግር ኳስ ተጫዋቾች በድሉ ውስጥ የጎላ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። ይህም ስፖርቱ የሕዝቦችን ወንድማማችነት እንዴት እንዳጠናከረ የሚያሳይ ሕያው ምስክር ነው።
ታሪክ ቅርጹን ይለውጣል እንጂ አይሞትም! ትናንት በአንድ ሀገር ጥላ ሥር ሕዝቦችን በስፖርት እና በስታዲየም ፍቅር ያቀራረበው 'ቀይ ባሕር'፣ ዛሬ ለኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው እና በኢኮኖሚው መድረክ ትልቅ ሀገራዊ የሕልውና ጥያቄ ሆኖ ብቅ ብሏል።
ኢትዮጵያ እያሳየች ያለችውን የሕዝብ ቁጥር ማደግ እና ፈጣን የኢኮኖሚ ፍላጎት ለማስቀጠል፣ የቀይ ባሕር ተጠቃሚነት እና የባሕር በር ተደራሽነት አማራጭ የሌለው ስትራቴጂያዊ ጉዳይ ነው።
ይሁንና ይህ የዘመናችን የባሕር በር ጥያቄ ታሪካዊ ስሜትን መሠረት ያደረገ ሳይሆን በቀጣናዊ ትሥሥር፣ በጋራ ተጠቃሚነት እና በዘላቂ ሰላም መርሕ ላይ የተመሠረተ የዲፕሎማሲ ውይይትን የሚጠይቅ ነው።
የኢትዮጵያን የቀይ ባሕር ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ለሀገራችን ኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን ለስፖርቱ ዘርፍም አዲስ በር ይከፍታል። ይህም በቀጣናው የሚፈጠር የኢኮኖሚ ትሥሥርን የሚያንሰራራ እና የስፖርት ቱሪዝምን የሚያስፋፋ አዲስ የተስፋ ወጋገን ነው።
የባሕር በር ጉዳይ የኢኮኖሚ፣ የንግድ እና የዲፕሎማሲ ውይይት ማዕከል ሆኖ ቢቀጥልም፤ ለብዙ የስፖርት አፍቃሪዎች ግን ይህ ስም ያለፈውን የጋራ የስፖርት ታሪክ እና ሕዝቦችን የማስተሣሠር ኃይሉ ይናፍቃቸዋል፤ ያም የትናንት ወርቃማ ትዝታ ዛሬም በቀጣናው ሕዝቦች መካከል ለሚፈጠር ዘላቂ የሰላም፣ የጋራ ተጠቃሚነት እና የኢኮኖሚ ትሥሥር ጠንካራ መሠረት እንዲሆን በጽኑ ይመኛሉ።
በእርግጥም የቀይ ባሕር ታሪክ በኢትዮጵያ ማኅደር ውስጥ ከእግር ኳስ ሜዳው ስሜት ተጀምሮ፣ ዛሬ እስከ አህጉራዊ የጂኦ-ፖለቲካ ውይይት ድረስ የተዘረጋ ነው። ቀይ ባሕር ትናንት በስታዲየሞች የፉክክር እና የድል ምልክት ነበር፤ ዛሬ ደግሞ የፍትሐዊ ተጠቃሚነት እና የጋራ ዕድገት ዋና አጀንዳ ሆኗል።
ትናንት በስፖርት ያገናኘን ታሪክ፣ ዛሬ ለቀጣናው ሀገራት የጋራ ዕድገት፣ የሰላም እና የፍትሐዊነት መግቢያ በር ይሁን!
በአዲስ የሺዋስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: