Search

የዓለምን የኃይል ሚዛን የለወጠው ብሪክስ እና የኢትዮጵያ አዲስ ስትራቴጂካዊ ከፍታ

ሓሙስ ሐምሌ 23, 2018 95

ለዘመናት ዓለምን በበላይነት ሲመራ የቆየው የአንድ ዋልታ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ የበላይነት አሁን ላይ ከፍተኛ የመዋቅር መናጋት እያጋጠመው ይገኛል።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማክተም በኋላ የተዘረጉት እንደ ዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ያሉ ተቋማት የታዳጊ አገራትን የልማት ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ማስተናገድ ባለመቻላቸው፣ የደቡቡ ዓለም አገራት አማራጭ ምህዳር እንዲፈልጉ አስገድዷቸዋል።

በዚህ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ምህዳር ውስጥ በጥብቅ እያደገ የመጣው ስብስብ ብሪክስ፣ የዓለም አቀፉን የኃይል ሚዛን በመቀየር ለአዳጊ ኢኮኖሚዎች አዲስ ተስፋ እና እውነተኛ አማራጭ ይዞ መጥቷል።

የብሪክስ አገራት የበለፀጉ አገራትን ኢ-ፍትሃዊ የገበያ ማግለል ፖሊሲ አጥብቀው የሚቃወሙ ሲሆን፣ ሁሉንም ያካተተ ፍትሃዊ የዓለም ሥርዓት ለመገንባት አዲሱን የልማት ባንክ በማቋቋም ታዳጊ አገራት ያለ ፖለቲካዊ ጣልቃ-ገብነት እና ቅድመ-ሁኔታ የፋይናንስ ምንጭ የሚያገኙበትን በር በሰፊው ከፍተዋል።

በዚህ ታሪካዊ የኃይል እና የኢኮኖሚ ሽግግር ወቅት ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ በዓለም አቀፍ ምህዳር ያላትን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ ትልቅ ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው።

የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ የሆነችው ሀገራችን፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጠና እድሎችን ከብሪክስ አገራት ጋር ለማስተሳሰር የሚያስችል የዲፕሎማሲ እና የኢኮኖሚ ድልድይ ሆና በመንቀሳቀስ ላይ ትገኛለች።

ይህ አባልነት በሀገር ውስጥ ለሚከናወኑ የኢንዱስትሪ፣ የግብርና፣ የታዳሽ ኃይል እና የዲጂታል ኢኮኖሚ ኢንቨስትመንቶች ሰፊ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ሽግግር እድል ከማመቻቸቱም በላይ፣ በብሔራዊ ገንዘብ የሚደረጉ የንግድ ልውውጦችን በማስፋፋት በሀገር ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ዝውውር ላይ የሚታዩ ጫናዎችን ለመቀነስ አዲስ የፋይናንስ አማራጭ ከፍቷል።

የብሪክስ መጠናከር የዓለም አቀፉን የኢኮኖሚ ማዕከል ወደ አዳጊ አገራት እያዞረው ባለበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት፣ ኢትዮጵያ በስብስቡ ውስጥ የምታደርገው ንቁ እና ስትራቴጂካዊ ተሳትፎ ሀገራዊ የልማት ግቦቿን ለማሳካት፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ምሶሶ ሆኖ ያገለግላል።

በሰለሞን ገዳ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: