Search

ሲኤንኤን (CNN) ስለ ኢትዮጵያ በአግራሞት የዘገበው ምንድን ነው?

ረቡዕ ሐምሌ 29, 2018 70

ዓለም አቀፉ የመገናኛ ብዙኃን ተቋም ሲኤንኤን (CNN) "ኮኔክቲንግ አፍሪካ" በተሰኘው ልዩ ዝግጅቱ ኢትዮጵያ ቡናን ወደ ውጭ ከመላክ ባለፈ ኢኮኖሚዋን በማብዛት በማዕድን፣ በታዳሽ ኃይል፣ በቱሪዝምና በግዙፍ መሰረተ ልማቶች ላይ እያደረገች ያለውን አስደናቂ ኢንቨስትመንት በአግራሞት ዘግቧል።

ሲኤንኤን በዘገባው እንዳመለከተው፣ ወደ 140 ሚሊዮን የሚጠጋና አብዛኛው ወጣት የሆነ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባን ከመለወጥ ጀምሮ በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑት ታላላቅ ኢኮኖሚዎች ተርታ ለመሰለፍ እያደረገች ያለው ጉዞ እጅግ አስገራሚ ነው።

ሚዲያው አትኩሮቱን ካደረገባቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አንዱ ሲሆን፣ ሲኤንኤን እንደዘገበው ይህ በአፍሪካ ትልቁ የውሃ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከባህር በር ርቆ የሎጂስቲክስ ፈተናዎችን አልፎ የተገነባ የኢንጂነሪንግ ድንቅ ስራ ነው።

ተቋሙ አክሎም፣ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለውና ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የፈጀው ይህ ግድብ፣ ምንም አይነት የውጭ እርዳታ ሳይታከልበት በኢትዮጵያውያን የገንዘብ አስተዋጽኦ ብቻ መገንባቱ አስገራሚ መሆኑን ዘግቧል።

ግድቡ በአሁኑ ወቅት 6 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ቤቶችን በኤሌክትሪክ ኃይል ከማገናኘት ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት ኃይል እያቀረበ መሆኑንና ለቱሪዝም መስህብነት የሚውሉ 72 ደሴቶችን መፍጠሩን ሲኤንኤን አብራርቷል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ ልዕለ ኃያል ለመሆን እያደረገች ያለውን ጥረት ሲኤንኤን አድንቋል።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘው የኩርሙክ የወርቅ ፕሮጀክት የሀገሪቱን ታሪክ እየቀየረ መሆኑን ሲኤንኤን ዘግቧል።

እንደ ሚዲያው ዘገባ ከሆነ፣ ይህ ፕሮጀክት ጥሬ ወርቅን ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ በስፍራው በሚገነባ ፋብሪካ በማቀነባበር በዓመት እስከ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝ ይጠበቃል።

ወርቅ የሀገሪቱ ቀዳሚ የውጭ ምንዛሬ አስገኚ በመሆን ታሪካዊውን የቡና ኤክስፖርት መብለጡንም ሲኤንኤን በአግራሞት ተመልክቶታል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እያደረገ ያለውን ዓለም አቀፍ መስፋፋት በተመለከተም ሲኤንኤን በዘገባው ሰፊ ሽፋን ሰጥቷል።

አሁን ያለው የአዲስ አበባ አየር መንገድ በዓመት 25 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅሙ ጣሪያ ላይ እየደረሰ በመሆኑ፣ ከዋና ከተማዋ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በቢሾፍቱ ከተማ 12 ቢሊዮን ዶላር የሚፈጅ አዲስ ሜጋ ኤርፖርት እየተገነባ መሆኑን ዘግቧል።

ይህ አየር መንገድ ሲጠናቀቅ በዓመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረው የገለጸው ሲኤንኤን፣ የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠናን ዕውን ለማድረግና ቪዛ አልባ የጉዞ ስርዓትን በአህጉሪቱ ለማስፋፋት ተቋሙ ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን መናገራቸውን አክሎ ገልጿል።

ሲኤንኤን እንዳለው፣ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ጸጋ ለዓለም ለማስተዋወቅ በቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ መነቃቃት ውስጥ ትገኛለች።

በተለይም በቅርቡ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ ሀገሪቱ ያላትን አስደናቂ የተፈጥሮ ቅርስ እና የስነ-ምህዳር ቱሪዝም አቅም በተጨባጭ የሚያሳይ መሆኑንና በርካታ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን ለመሳብ የሚያስችል ያልተነካ ሀብት መሆኑን ሚዲያው በዘገባው አስገንዝቧል።

በጌቱ ላቀው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: