Search

ሌሊቱ ሲጀምር አዲስ የቱሪዝም ዓለም ይነቃል

ረቡዕ ሐምሌ 29, 2018 49

በቀን ውብ ተራራን፣ ሸለቆን እና ወንዝን ጎብኝተው፤ ሌሊት ግን ሰማይን ለመጎብኘት አስበው ያውቃሉ? 

ይህን ጥያቄ የሚመልሰው "የሌሊት ሰማይ ቱሪዝም" (Dark Sky Tourism) ሲሆን፣ በሰው ሰራሽ ብርሃን ያልተሸፈነ ሰማይን አረፍ ብሎ የከዋክብት ስብስብለመመልከት፣ የተፈጥሮን ጸጥታ ለመስማት እና ከሰማይ ጋር ለመወያየት የሚደረግ ድቅድቅ የሌሊት ጉዞ ነው። 

ዓለማችን በዚህ ዘርፍ በፍጥነት እያደገች ሲሆን፣ ዘላቂ ቱሪዝምን፣ የተፈጥሮ ጥበቃን እና የገጠር ኢኮኖሚን ለማጠናከር አዲስ አጋጣሚ ሆኗል።

ኢትዮጵያም በዚህ ዘርፍ እጅግ የታደለች ናት። የሴሜንና የባሌ ተራሮች፣ ዳናኪል፣ ነጭ ሳር እና ከከተማ ብርሃን የራቁ በርካታ የተፈጥሮ መዳረሻዎች በቀን በተፈጥሮ ውበታቸው እንደሚማርኩ ሁሉ፣ በሌሊትም ለኮከብ ምልከታ የሚሆኑ ድንቅ ቦታዎች ናቸው።

የዚህ ቱሪዝም ጥቅም የሰማይን ውበት ከማየት ባሻገር የሌሊት ሕይወት ላላቸው እንስሳት ምቹ ሁኔታን ከመፍጠሩ በላይ ለሰዎች የአዕምሮ ዕረፍትን ይሰጣል። በተለያዩ ሀገራት የጨለማ ሰማይ መዳረሻዎች የገጠራማ ማህበረሰቦችን አካባቢያዊ ኢኮኖሚ እንዳነቃቁ ጥናቶች ያሳያሉ።

በሀገራችን አዲስ የኢኮኖሚ ሞተር የሆኑ በርካታ የኮሪደር ልማቶች የከተሞቻችንን ገጽታ እየቀየሩ በመሆናቸው፣ በርካታ ጎብኚዎች ወደ እነዚህ ፓርኮችና ሎጆች እየጎረፉ ይገኛሉ። በቀን እነዚህን ስፍራዎች የሚጎበኘው ቱሪስት፣ ማታ ደግሞ ከዋክብትን ለመቁጠር የሚቆይበትና ተመልሶ ምቹ በሆኑ ውብ ሎጆች የሚያርፍበት ዕድል ተፈጥሯል።

ከከተማ ብርሃን የራቁ ከፍተኛ ተራሮች፣ ሰፊ ሜዳዎችና የተፈጥሮ ፓርኮች ያሏት ሀገራችን፣ ይህን አዲስ የቱሪዝም ዘርፍ በአፍሪካ መሪ ተጠቃሽ ሆና ለመምራት ትልቅ እድል አላት።

ሌሊትን እንደ ሀብት ማየት ከቻልን፣ ሰማዩ ራሱ ድንቅ የቱሪዝም መዳረሻ ይሆናል። 

ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ የሚያስደንቀን ውበት ከመሬት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ከራሳችን በላይ በተዘረጋው ሰፊ ሰማይ ላይ ይገኛልና።

በልዩ እሸቱ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: