የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ሒደት ሐሳቦች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተሰባስበው ወደ አንድ ማዕከል የሚመጡበት፣ እጅግ ወሳኝ እና ታሪካዊ ወደ ሆነ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። ይህ የሽግግር ምዕራፍ የሐሳብ ልዩነቶችን የማረቅ፣ የተራራቁ የፖለቲካ ጠርዞችን የማቀራረብ እና ዘላቂ መግባባትን የመፍጠር ጥበብ በተግባር የሚፈተንበት የዴሞክራሲ ማሕፀን ነው።
በዓለማችን እጅግ የሠለጠኑ የዴሞክራሲ ልምምድ ባለባቸው ሀገራት፣ የፖለቲካ ስኬት የመጨረሻው ጣሪያ ተደርጎ የሚወሰደው ይህንን የተቃራኒ ሐሳቦች መጋጨት ሒደት በብልሃት አልፎ ወደ ሀገራዊ ስምምነት የመሸጋገር ጥበብ ነው። የእውነተኛ ዴሞክራሲ ሕያው ትርጉም የሚገለጠውም እዚህ የፈተና መድረክ ላይ ነው።
ለመወያየት በጠረጴዛ ዙሪያ መቀመጥ አንድ ትልቅ ሀገራዊ እርምጃ መሆኑ አያጠያይቅም። ይሁን እንጂ፣ የውይይቱ ስኬት የሚለካው "የሰጥቶ መቀበል" (Give and Take) መርህን በተግባር በማዋል ልክ ነው። በአንድ ጣራ ሥር፣ በአንድ ሀገር ውስጥ አብረን ለመኖር ከወሰንን፣ የግድ ሁላችንንም የሚያግባባን "የወል እውነት" (Shared Truth) ማዋለድ ይጠበቅብናል።
የወል እውነት የሚወለደው እያንዳንዱ ተሳታፊ "የእኔ ሐሳብ ብቻ ይፈጸም" ከሚል ግትር አቋሙ ወርዶ፣ ከሌላውም ወገን ሐሳብ ሲካፈል እና አንድ የሚያደርገውን የጋራ ክር ሲፈልግ ብቻ ነው። "እኔ ያልኩት ካልሆነ ወይም ሞት" የሚለው ጽንፈኛ አቋም፣ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሒደት ውስጥ እጅግ ደካማው እና አፍራሹ መንገድ መሆኑን መገንዘብ ያሻል።
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የዴሞክራሲ እና የምክክር ምሁራን ጥልቅ ትንታኔ ይሰጣሉ። ታዋቂው የፖለቲካ ፈላስፋ ዩርገን ሀበርማስ "ተግባቦታዊ ድርጊት" በሚለው ፅንሰ ሐሳቡ፣ እውነተኛ መግባባት የሚፈጠረው ተሳታፊዎች የራሳቸውን ጠባብ ቡድናዊ ፍላጎት ትተው በምክንያታዊ የሐሳብ ልውውጥ የጋራ እውነት ላይ ለመድረስ ሲተጉ መሆኑን ይገልጻል።
በተመሳሳይ፣ አረንድ ሊጅፋርት የ"ምክክራዊ ዴሞክራሲ" (Consensus Democracy) ሞዴልን ሲያብራሩ፣ በልዩነቶች የተሞሉ ማኅበረሰቦች ሊድኑ የሚችሉት አሸናፊ እና ተሸናፊ በሚፈጥር አብላጫ ድምፅ ሳይሆን፣ ሁሉንም በሚያካትት የወል ስምምነት ነው በማለት ያስምሩበታል።
ከሀገራት ተሞክሮ ስንመለከት፣ እንደ ደቡብ አፍሪካ በ"ኮዴሳ" (CODESA) የሽግግር ውይይቶች ወይም እንደ ሰሜን አየርላንድ የ"መልካም አርብ ስምምነት" (Good Friday Agreement) ያሉ ሒደቶች የተሳኩት፣ ተሳታፊዎቹ መሠረታዊ እና የጋራ የሆኑ ግቦችን ለይተው በማጽደቅ፣ ወዲያው መፍታት ያልቻሉትን ውስብስብ ልዩነቶች ደግሞ ለጊዜው እያቆዩ በሒደት ለማረቅ በመስማማታቸው ነው። ጥበቡ ያለው እዚህ ላይ ነው። ሰዎች በተለያየ አቅጣጫ እየተጓዙ ቢመጡም፣ ሰው በመሆናቸው እና የጋራ ሀገር ስላላቸው ብቻ የሚያጋሯቸው መሠረታዊ ፍላጎቶች አሏቸው። በመሠረታዊ ግቦች ላይ ከተግባቡ፣ የቀረውን እያረቁ የመሄድ ብስለትን ማሳየት የሠለጠነ ፖለቲካ መገለጫ ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን በረዥም ታሪካችን ያዳበርነው፣ አብሮነታችንን ያቆየ እና የፈተና ዘመናትን የተሻገርንበት የራሳችን የሆነ ደማቅ የወል እውነት አለን። አሁን የሚጠበቅብን ይህንን በውስጣችን ያለውን የወል እውነት፣ ከአዲሱ ዘመን ፖለቲካዊ ፍላጎቶች ጋር አዋህደን በምክክር አውድማ ላይ በድጋሚ ማዋለድ ነው።
ስለሆነም፣ ይህ የወል እውነትን የማዋለድ ጉዞ የጥቂቶች ኃላፊነት አይደለም። ይህንን የሀገርን ኅልውና የማጽናት እና የነገዋን ኢትዮጵያ በጸና መሠረት ላይ የማቆም ሒደት ስኬታማ ለማድረግ፣ መላው ሕዝብ እና ልሂቃን ከምክክር ሒደቱ ጎን በመቆም የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል። ግትርነትን አውልቀን፣ የመደማመጥን ካባ ለብሰን፣ የሁላችንም የሆነችውን ታላቋን ኢትዮጵያ የወል እውነት በጋራ እናዋልድ!
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: