ዓለም አቀፉ የመገናኛ ብዙኃን ተቋም ሲኤንኤን (CNN) ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ ልዕለ ኃያል ለመሆን እያደረገች ያለውን ጥረት እና ግዙፍ ፕሮጀክቶቿን በተመለከተ ሰፋ ያለ ዘገባ አቅርቧል።
ሲኤንኤን በዘገባው እንዳመለከተው፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘው የኩርሙክ የወርቅ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት ትላልቅ የማዕድን ኢንቨስትመንቶች መካከል ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል።
የካናዳው አላይድ ጎልድ ኮርፖሬሽን የሚያስተዳድረው ይህ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ግዙፍ የወርቅ ማውጫ መሆኑን ተቋሙ ዘግቧል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች እና አሳሾች በምዕራብ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ተራሮች ስር የሚገኘውን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚያወጣ የወርቅ ክምችት ለማውጣት ሌት ተቀን እየሰሩ እንደሚገኙም ጣቢያው በዘገባው አካቷል።
እንደ ሲኤንኤን ዘገባ ከሆነ፣ በዚህ ስፍራ የሚገኘው ወርቅ ከፍተኛ ካራት ያለው እና ጥራቱን የጠበቀ ነው። ዋና ጂኦሎጂስት ምህረት አበበ ለጣቢያው እንደገለጹት፣ ወርቁ ከሌሎች ማዕድናት ጋር ሳይቀላቀል በኳርትዝ አለቶች ውስጥ የሚገኝ ረቂቅ ወርቅ በመሆኑ አለቶቹን በመሰብሰብ፣ መለያ ቁጥር በመስጠት እና በመፍጨት ከፍተኛ የፍለጋ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
ሲኤንኤን አክሎም፣ ይህን ፕሮጀክት ልዩ የሚያደርገው ወርቁን በውጭ ሀገር ከማስጠራት ይልቅ በስፍራው ላይ በሚገነባ ግዙፍ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በሀገር ውስጥ የሚመረት መሆኑን አትቷል።
በዚህም ፋብሪካ በዓመት 290 ሺህ አውንስ ወይም 10 ቶን ወርቅ ለማምረት የታቀደ ሲሆን፣ አሁን ባለው የገበያ ዋጋ ወደ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝ ይጠበቃል።
በቅርቡ ወደ ምርት የሚገባው ይህ ፕሮጀክት፣ ወርቅ ቡናን በመብለጥ የኢትዮጵያ ቀዳሚ የውጭ ምንዛሬ አስገኚ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ሲኤንኤን አብራርቷል።
ለዚህም በማሳያነት በ2024/2025 በጀት ዓመት የመጨረሻ ሩብ ዓመት የቡና ወጪ ንግድ 1.1 ቢሊዮን ዶላር ሲያስገኝ፣ ወርቅ ግን ወደ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘቱን ዘገባው አመላክቷል።
ከማዕድን ዘርፉ ባለፈም ሲኤንኤን የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን የሚያሳዩ ተጨማሪ አቅሞችን በዘገባው ዳስሷል።
በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኙ ብርቅዬ ማዕድናት፣ በምዕራቡ ክፍል የሚገኙት ፖታሽ፣ መዳብ እና ሌሎችም ማዕድናት እንዲሁም መንግስት ያደረገው አዲሱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የፋይናንስ ዘርፉ ክፍት መሆን ለውጭ ባለሀብቶች ትልቅ መተማመንን መፍጠሩን ዘግቧል።
በጌቱ ላቀው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: