የነዳጅ አውቶቡሶችን ወደ ፈሳሽ ተፈጥሮ ጋዝ የሚቀየር ቴክኖሎጂ የኢትዮጵያን አረንጓዴ የትራንስፖርት ሽግግር እንደሚያፋጥን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ ገለጹ።
በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ግሩፕ ቢሾፍቱ ሞተር ቬሂክልስ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪን የጎበኙት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ተቋሙ ከFRANKUN ሀገር በቀል ድርጅት ጋር በመተባበር በነዳጅ የሚሰሩ አውቶቡሶችን ወደ ተፈጥሯዊ ጋዝ (LNG) የሚቀይር ቴክኖሎጂ ማልማቱ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ኢነርጂ እና የዘላቂ ትራንስፖርት ሽግግር የሚያፋጥን መሆኑን ተናግረዋል።
በአፍሪካ ደረጃ የመጀመሪያ የሆነው ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ (LNG) መቀየሪያ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ኢትዮጵያ ወደ አረንጓዴ እና ዘላቂ የትራንስፖርት ሥርዓት የምታደርገውን ሽግግር በማፋጠን፣ በነዳጅ ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ፣ የውጭ ምንዛሪን ለመቆጠብ እና የካርቦን ልቀትን በመቀነስ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የማኑፋክቸሪንግ፣ የአውቶሞቢል አገጣጠም፣ የቴክኖሎጂ ልማት እና የሰው ኃይል አቅም በተግባር ተመልክተዋል።
ተቋሙ ሀገራዊ ተልዕኮውን ከዘመናዊ ኢንዱስትሪ እና ከአረንጓዴ ቴክኖሎጂ ጋር በማጣመር ወደ አዲስ የልማት ምዕራፍ መሸጋገሩንም አድንቀዋል።
ይህ ፕሮጀክት በ“አረንጓዴ ዐሻራ” እና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስቀመጡትን ሀገራዊ አቅጣጫ በተግባር የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ኢትዮጵያን ከከፍተኛ የነዳጅ ጥገኝነት ወደ ታዳሽ እና ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት ተጠቃሚነት ለማሸጋገር የተቀመጠውን ስትራቴጂ እንደሚደግፍ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: