በቤኒን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና የፈጠራ ሚኒስትር ማሁና አክፕሎጋ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እያደረገ ይገኛል።
ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ወቅት፣ ኢትዮጵያ የካበተ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተሞክሮዋን ለአህጉሪቱ ለማካፈል የምታደርገው ጥረት፣ የዲጂታል ዲፕሎማሲዋ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣቱን የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
የልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ በነበረው ቆይታ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን እንዲሁም የ“ፋይዳ” ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት የሥራ እንቅስቃሴዎችን ተመልክቷል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተለያዩ የመንግሥት አሠራሮችን በአንድ ቋት በማስተናገድ ለአገልግሎት ፈላጊዎች የፈጠረውን ቀልጣፋና ዘመናዊ አሠራር የልዑካን ቡድኑ አባላት አድንቀዋል።
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ፣ የዜጎችን ደኅንነቱ የተጠበቀ መረጃ በማደራጀትና ለኢትዮጵያ የዲጂታል ምህዳር መስፋፋት የጣለውን ጠንካራ መሠረት መመልከታቸውም ተገልጿል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እያከናወነች ያለችው አጠቃላይ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ለአፍሪካ ሀገራት ትልቅ አርአያና መማሪያ የሚሆን መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በተለይም አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል ሥርዓት በመቀየር፣ የመንግሥት አሠራርን በማቀላጠፍና የዜጎችን እንግልት በመቀነስ ረገድ የተከናወኑ ተግባራት የሚደነቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ጉብኝቱ ሁለቱ ሀገራት በዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በፈጠራ እና በመረጃ ልውውጥ ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነትና ትብብር የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑ ተገልጿል።
በሳምሶን በላይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: