በኢትዮጵያ በስፋት ሳይለመድ የቆየውና ከፍተኛ የድርቅ መቋቋም አቅም ያለው የካሳቫ ሰብል፣ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የማስገኘት እምቅ አቅም እንዳለው ጥናቶች ያመለክታሉ።
ከቁልቋል ቤተሰብ የሚመደበውና ከ200 በላይ ዝርያዎች ያሉት ይህ ሰብል፣ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ምዕራብ አፍሪካ እንዲሁም በ18ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ወደ ምስራቅ አፍሪካ የገባ ታሪካዊ ተክል ነው።
የግብርና ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚያሳዩት ካሳቫ ማዳበሪያ የማይፈልግ፣ በአእዋፋት፣ በተባዮችና በዱር እንስሳት የማይጠቃ እንዲሁም እጅግ አነስተኛ እንክብካቤ የሚሻ ድንቅ ሰብል ነው።
ከዚህም በላይ መሬት ውስጥ እስከ ሁለት ዓመታት ቢቆይ እንኳ የማይበላሽ ሲሆን፣ በተመናመነና አሲዳማ በሆነ መሬት ላይ ከፍተኛ ምርት የመስጠት ብቃት ስላለው እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋሙ "የጽናት ሰብል" በመባል ይታወቃል።
ካሳቫ በውስጡ ባለው ከፍተኛ የካርቦሃይድሬት ይዘት በኃይል ሰጪነቱ ከሥራ-ሥር ሰብሎች ሁሉ ተወዳዳሪ የለውም። ተቀቅሎ ከመበላቱ ባሻገር ደርቆና ተፈጭቶ እንደ ጤፍ ካሉ እህሎች ጋር በመደባለቅ ለእንጀራ፣ ለብስኩት፣ ለቂጣ፣ ለገንፎ፣ ለወጥ እና ለሾርባ ዝግጅት በስፋት ይውላል።
የስሩ ተረፈ-ምርት እና በፕሮቲን የበለጸገው ቅጠሉ ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ ሲሆን፣ ከዚህም ባሻገር ለጨርቃጨርቅ፣ ለወረቀት፣ ለመድኃኒት እንዲሁም ለምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪዎች በዋና ግብዓትነት ያገለግላል።
ሰብሉ ከባህር ወለል በላይ እስከ 4,000 ሜትር ከፍታ ባላቸው የኢትዮጵያ ሥነ-ምህዳሮች በሙሉ ማደግ የሚችል መሆኑ ደግሞ ሌላው ልዩ ተፈጥሯዊ ጸጋው ነው።
በአሁኑ ወቅት በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በሲዳማ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ለምግብነት ያለው ተፈላጊነት እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ አርሶ አደሮችም በውስን መሬት ላይ ብዙ ምርት እያመረቱ ይገኛሉ።
ሰብሉ ያለውን ድርቅን የመቋቋም አቅም እና እያደገ የመጣውን ተፈላጊነት በመገንዘብም በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በአማራ ልማት ማህበር አማካኝነት ዘሩን ለአርሶ አደሮች በማሰራጨት ለማላመድ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።
ሰብሉን በምርምር በተደገፈ መልኩ ለማሳደግ የሚደረጉ ጥረቶች ተስፋ ሰጪ ቢሆኑም፣ በሰፋፊ ማሳዎች ላይ በስፋት የማምረት ሂደቱ ግን አሁንም ተጨማሪ ስራ ይፈልጋል።
የካሳቫን እምቅ አቅምና አዋጭነት መሠረት በማድረግ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮችና ባለሀብቶች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስልቶችን በመተግበር፣ ሰብሉን በስፋት በማምረት ለበርካቶች የሥራ እድል መፍጠር ይቻላል።
የተቀነባበረ የካሳቫ ዱቄት እና ስታርች ወደ ውጭ በመላክም ኢትዮጵያ አዲስ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ማግኘት እንደምትችል በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያመላክታሉ።
በመሀመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: