Search

ኢትዮጵያ በምክክር መንገድ፤ ከቅሬታ ወደ ይቅርታ፣ ከልዩነት ወደ የጋራ ራዕይ

ሓሙስ ሐምሌ 23, 2018 108

ሀገራት በታሪካቸው ዘመናትን የተሻገሩ ውስብስብ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ታሪካዊ ስብራቶች ያጋጥሟቸዋል። እነዚህን ፈተናዎች ዘላቂ በሆነ መንገድ የመፍታትና ወደ ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ የማሸጋገር መሠረታዊ መንገድ ደግሞ ግልጽ፣ አሳታፊ እና እውነተኛ ሀገራዊ የምክክር መድረክ መፍጠር ነው።

በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በመካሄድ ላይ የሚገኘው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤም የዚሁ ታሪካዊ ጥረት አካል እና የጋራ መግባባት ፍለጋ ትልቅ ማሳያ ነው።

የምክክር ጉባኤ መድረኩ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን፣ የፖለቲካ ኃይሎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የሴቶችና ወጣቶች ተወካዮችን እንዲሁም የሲቪክ ማኅበራትን በአንድ ጥላ ስር ያሰባሰበ ነው።

የመድረኩ ዋና ዓላማም ከዚህ ቀደም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የነበሩ የሐሳብ ልዩነቶችን በሠለጠነ መንገድ በመወያየት ወደ እውነተኛ የጋራ መግባባት መሸጋገር ነው።

ምክክሩ በርካታ የማኅበረሰብ ተወካዮች ድምፃቸውንና ዕይታቸውን ያለ ምንም ስጋት የሚያንጸባርቁበት ነፃ የሐሳብ ማንሸራሸሪያ በመሆኑ፣ ለዘመናት ተከማችተው የቆዩ ቅሬታዎችን በንግግር ለመፍታት ከማስቻሉም በላይ፣ የወደፊት ሀገራዊ አቅጣጫችንን በጋራ ለመቃኘት አዲስ መንገድ ይከፍታል።

በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ላይ የሚነሱ ሐሳቦችና የሚካሄዱ ውይይቶች የሚያሳዩት አንድ ትልቅ እውነት፣ ልዩነቶቻችንን እንደ ውበትና ጥንካሬ እንጂ እንደ ጠበኝነትና መለያየት የማንመለከትበት አዲስ የፖለቲካ ባህል እየተገነባ መሆኑ ነው።

በጉባኤው ላይ በሚነሱ አጀንዳዎች ዙሪያ የሚደረጉ ከባድና የሰረፁ ውይይቶች፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለገጠሟት ዘመናት ለተሻገሩ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለማስገኘት የተነደፉ ናቸው።

የምክክር ሂደቱ ስኬት የሚለካውም በተደረሱ ስምምነቶች ብዛት ብቻ ሳይሆን፣ አዳምጦ የመረዳት እና የሌላውን ዕይታ የማክበር ባህል በመካከላችን ማስረፅ በመቻሉ ነው። በአዲስ አበባ እየተካሄደ የሚገኘው ይህ ጉባኤ፣ ለቀጣዮቹ የሀገራችን ክልላዊና ሀገራዊ ውይይቶች ጠንካራ መሠረትና አዎንታዊ ማዕበል የመፍጠር አቅም አለው።

ይህ የምክክር ጉባኤ ፍጻሜው የሚያደርሰው በውይይት የተደገፉ ሀገራዊ መግባባቶችና ምክረ-ሐሳቦች ላይ ነው።

እነዚህ ውጤቶችም፣ ለዘላቂ ሰላም መሠረት በመጣል በፖለቲካና በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ የሚነሱ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍቻ ሥርዓትን ይዘረጋሉ፣ የሕዝብ አመኔታ ያላቸው እና ፍትሃዊ የሆኑ ሀገራዊ ተቋማትን ለመገንባት መንገድ ይጠርጋሉ እንዲሁም የጋራ ሀገራዊ ራዕይ በመቅረጽ ሕዝቡ የኔ የሚለውና የሚተገብረው የወደፊት ሀገራዊ ግብና ራዕይ እንዲቀርፅ ያስችላሉ።

ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ሀገራችንን የወደፊት አቅጣጫ የሚወሰን ታሪካዊ አጋጣሚ ሲሆን፣ ልዩነቶችን ይዞ ወደ አንድነት፣ ቅሬታዎችን ይዞ ወደ ይቅርታ እና መከፋፈልን አስወግዶ ወደ ጋራ መግባባት ለመሸጋገር የተከፈተ ትልቅ የታሪክ ደጃፍ ነው።

የዚህ መድረክ ስኬት የሁሉም ዜጋ ንቁ ተሳትፎ፣ በጎ ፈቃድ እና የጋራ ኃላፊነት የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ውጤቱ ለነገዋ ኢትዮጵያ የፀና መሠረት እንደሚሆን የታመነ ነው።

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: