Search

የአማራ ክልል ምክር ቤት 12ኛ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ

ሓሙስ ሐምሌ 23, 2018 101

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 5ኛ የሥራ ዘመን፣ 12ኛ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል።

የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋንቱ ተስፋዬ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ ምክር ቤቱ ባለፉት አምስት ዓመታት የሕዝብ ተወካዮች የወከሏቸውን ዜጎች ድምፅ በማንፀባረቅ በኩል የነበራቸው ሚና ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።

በተጨማሪም በክልሉ የሚቀርቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ዕቅዶች ተፈፃሚነት እንዲኖራቸው የአባላቱ ክትትልና ቁጥጥር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልፀዋል።

አፈ ጉባኤዋ አክለውም፣ ባሳለፍነው በጀት ዓመት በክልሉ የሚታዩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመሻገር የተነደፈው የ25 ዓመት አሻጋሪ የልማት ዕቅድ ወደ ትግበራ መግባቱንና አዎንታዊ ውጤቶችንም ማሳየት መጀመሩን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል፣ በክልሉ የሚታዩ ግጭቶችና ችግሮች አካባቢውን ወደኋላ እየጎተቱት መሆኑን አፈ ጉባኤዋ ገልፀዋል። እነዚህ ችግሮች የክልሉን የመልማት አቅም በእጅጉ እየጎዱት በመሆኑ፣ አለመግባባቶችን በውይይትና በንግግር መፍታት "ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም" ብለዋል።

በቀጣይ ጊዜያት በክልሉ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን መስራት፣ በፍትህ አሰጣጥ ሂደት ላይ የዜጎች ተሳትፎ እንዲጎለብት ማድረግ፣ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የተዘረጉ የማሻሻያ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ መከታተል፣ የክልሉን የመልማት አቅም ለማሳደግ የገቢ አሰባሰብን ማጠናከርና ብልሹ አሰራሮችን በጋራ መከላከልን ጨምሮ የምክር ቤቱ አባላት ያላቸውን ሚና አጠናክረው እንዲቀጥሉ አፈ ጉባኤዋ ጥሪ አቅርበዋል።

ምክር ቤቱ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሀምሌ 26 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በሚኖረው የሶስት ቀን ቆይታ የ2018 በጀት ዓመት የአስፈፃሚ አካላትን የዕቅድ ክንውን፣ የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርቶች መርምሮ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በተጨማሪም በጉባኤው ላይ የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ የበጀት ዕቅድ ቀርቦ በሰፊው ከተመከረበት በኋላ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በሳሙኤል ወርቃየሁ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: