Search

ከ8 ሺህ በላይ አርሶ እና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የጨልጨል መስኖ ፕሮጀክት

ሓሙስ ሐምሌ 23, 2018 152

የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ባሌ እየተገነባ የሚገኘውን የጨልጨል መስኖ ፕሮጀክት ግንባታን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት እየተሠራ መሆኑን ገልጿል።

የሚኒስቴሩ የሥራ ኃላፊዎች እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የፕሮጀክቱን የግንባታ ሂደት ተመልክተዋል።

ፕሮጀክቱ በተቋራጭ የአቅም ውስንነትና በዲዛይን ለውጥ ምክንያት ተጓትቶ የቆየ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማስደገፍና አዲስ ተቋራጭ በመተካት የግንባታ ሥራው እንዲቀጥል መደረጉ ተገልጿል።

በሚኒስቴሩ የመስኖ ፕሮጀክቶች ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አሸናፊ ሊካሳ እንደገለጹት፣ የጨልጨል መስኖ ፕሮጀክትን አጠናቅቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ቀጥተኛ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ነው።

በ2012 ዓ.ም የግንባታ ሥራ የተጀመረው የጨልጨል መስኖ ፕሮጀክት በ2018 በጀት ዓመት መጨረሻ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት ታቅዶ እንደነበር አስታውሰው፣ በዲዛይን ችግርና በተቋራጭ የአቅም ውስንነት ምክንያት መጓተቱን አመልክተዋል።

የመስኖ ፕሮጀክቱ በተለይ በቅድመ-ዕቅዱ በአነስተኛ መስኖ ደረጃ ሊገነባ ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ የልማት አቅሙንና ደረጃውን ከፍ ለማድረግ በተደረገው የዲዛይን ማሻሻያ ምክንያት ግንባታው ለተወሰኑ ጊዜያት ቆሞ እንደነበር አንስተዋል።

እንዲሁም ከተቋራጭ የአቅም ውስንነት ጋር ተያይዞ ያጋጠመውን ችግር ለመቅረፍ፤ የነበረውን ውል በማቋረጥ በዘርፉ ልምድና አቅም ያለው ተቋራጭ ሥራውን እንዲቀጥል መደረጉን አስረድተዋል።

የጨልጨል መስኖ ፕሮጀክት በሁለት ሎት ተከፋፍሎ እየተገነባ መሆኑንና አንደኛው የግድቡ ግንባታ ሁለተኛው ደግሞ የመስኖ ካናል ዝርጋታ እንደሆነ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም 4 ሺህ 145 ሄክታር ማልማት የሚችለው የካናል ሥራ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የተጓተተውን የግድቡን ሥራ በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ለማስገባት ትኩረት መደረጉን ማብራራታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የፕሮጀክቱን ግንባታ በአዲስ መልክ እያከናወነ የሚገኘው የአለማየሁ ከተማ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ፕሮጀክት ማኔጀር ኢንጂነር ባህሩ ፊኖ በበኩላቸው፣ የፕሮጀክቱ አሁናዊ አፈጻጻም 50 በመቶ መጠናቀቁን ገልጸው፣ ለግድቡ የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ በበቂ ሁኔታ በመዘጋጀታቸው በ2019 የበጀት ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

የፕሮጀክቱ ግንባታ ሲጠናቀቅ 4 ሺህ 145 ሔክታር መሬትን በማልማት ከ8 ሺህ በላይ አርሶና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: