የኢትዮጵያ እና የአዘርባጃን የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ትብብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንና በቀጣይም ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዘርባጃን ሪፐብሊክ ብሔራዊ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ሳሂባ ጋፋሮቫ (ዶ/ር) አረጋገጡ።
አፈ-ጉባኤዋ ይህንን መልዕክት ያስተላለፉት በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በተዘጋጀ ልዩ የውይይት መድረክ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው።
በመድረኩ ላይ እንዳብራሩት፣ ሁለቱ ሀገራት በተለይም በትምህርት ዘርፍ፣ በዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥ እና በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ዙሪያ በርካታ ስኬታማ ስራዎችን በጋራ እያከናወኑ ይገኛሉ።
ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን ፈጣን ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ያደነቁት ሳሂባ ጋፋሮቫ (ዶ/ር) የአፍሪካ ዋና የዲፕሎማሲ ማዕከል በመሆን እየተጫወተች ያለውን የላቀ ሚና አድንቀዋል።
የተሻለ ነገን ለመፍጠር ሁልጊዜም በጋራና በትብብር መስራት ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት አፈ-ጉባኤዋ፣ ይህንን በጎ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የሁለቱን ሀገራት ሁለገብ ትስስር ይበልጥ ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።
በአባዲ ወይናይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: