Search

ከምግብ ዋስትና እስከ የዱር እንስሳት መጠለያ

ሓሙስ ሐምሌ 23, 2018 109

ኢትዮጵያ ዛሬን ለነገ፣ ነገን ደግሞ ለዛሬ በሚል ጥበብ የተሞላበት እሳቤ ለሰባተኛው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ ዘመቻዋ በታላቅ ዝግጅት ላይ ትገኛለች። ይህ ሀገራዊ እንቅስቃሴ ለምግብ ዋስትና፣ ለብዝኃ ሕይወት ጥበቃና ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ የተፈጥሮ ሀብት ግንባታን እውን ለማድረግ የተወጠነ ታላቅ እርምጃ ነው።

ባለፉት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት ተጀምሮ ዓለምን ያስደነቀውና "አይቻልም" የሚለውን አስተሳሰብ የሰበረው ይህ መርሃ ግብር፣ በሁሉም ኢትዮጵያውያን የተቀናጀ ክንድ የተካሄደና አሁን ላይ ዘላቂ ሀገራዊ ባህል ለመሆን የበቃ ንቅናቄ ነው።

"በጋራ ተስፋ እንተክላለን!" በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው የዘንድሮው ሀገር አቀፍ የችግኝ ተከላ ዘመቻ ለመጀመር አራት ቀናት ብቻ የቀሩ ሲሆን፣ የተደወለው ጥሪም ለሁሉም ኢትዮጵያውያን አንድ ግልጽ መልእክት አስተላልፏል፤ እርሱም ዛሬ በእጃችን የምንተክለው ችግኝ የነገዋ ሀገራችን የሕይወት ዋስትና መሆኑን እንድናስታውስ ነው።

የአረንጓዴ ዐሻራ ዓላማ ዛፎችን በመትከል ብቻ የሚገደብ ሳይሆን፣ በደን መራቆት ምክንያት መኖሪያቸውን ያጡ ብርቅዬ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳትና አዕዋፋት ወደ ተፈጥሯዊ መጠለያቸው እንዲመለሱ የማስቻያ መሠረት መጣል ጭምር ነው።

ይህ በጎ ጥረት እንደ ቀበሮ፣ የተራራ ንያላ፣ የምኒሊክ ድኩላ፣ የጭላዳ ዝንጀሮ፣ ዋልያ እንዲሁም እንደ ሰማያዊ ክንፍ ዝይ ያሉ ብርቅዬ አዕዋፋትና እንስሳት የሚኖሩባቸውን ጤናማ የደን ሥነ-ምህዳሮች ዳግም እንዲያንሰራሩ ያደርጋል።

ጎን ለጎንም ከማንጎ፣ አቮካዶና ፓፓያ ባሻገር እንደ ማካዳሚያ፣ ብሉ ቤሪ እና የፓሽን ፍራፍሬ ያሉ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን አዳዲስ ዝርያዎች በሰፊው በመትከል የትውልድን የምግብ ዋስትና፣ የገቢ ምንጭ፣ የቱሪዝም ሀብትና የብዝኃ ሕይወት በጋራ ያጎለብታል።

ሰኞ ዕለት በሚከናወነው የአንድ ጀምበር ዘመቻ የምንተክለው እያንዳንዱ ችግኝ የነገ የዱር እንስሳት መኖሪያ፣ የወፎች መጠለያ፣ የልጆቻችን ጣፋጭ ፍራፍሬ እና የኢትዮጵያ አረንጓዴ ተስፋ ይሆናል።

የአረንጓዴ ዐሻራ ነጋሪት ተሰምቷል፤ አሁን ደግሞ የእያንዳንዳችን እጅ ችግኝ ላይ የሚያርፍበት ታሪካዊ ወቅት ነው።

በልዩ እሸቱ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: