Search

ከምድር እስከ አየር፡- የኢትዮጵያ ድል ሠራዊት

ሓሙስ ሐምሌ 23, 2018 91

በ21ኛው ክፍለ ዘመን ወታደራዊ ሳይንስ፣ የጦርነት አውድ ከባህላዊው የሰው ኃይል ብዛት እና የምሽግ ትግል ወደ ቴክኖሎጂያዊ ልቅነት፣ ፈጣን ምላሽ ሰጪነትና የባለ-ብዙ አውድ ውጊያ ስልት ተሸጋግሯል።

በዚህ የስትራቴጂያዊ ሽግግር ማዕከል ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ ከአየር ተምዘግዝገው በሚወርዱ የቀይ ቦኔት ኃይሎች እና በዘመናዊ የካሚካዜ ቴክኖሎጂ አማካኝነት የጠላትን ስትራቴጂያዊ የስህበት ማዕከል በቅጽበት በማፈራረስ፣ የማይደፈር አዲስ የብረት አጥር በሰማይም በምድርም መገንባቷን በተግባር እያረጋገጠች ትገኛለች።

የሀገራችን የረዥም ጊዜ ታሪክ በግልጽ እንደሚያስረዳው ኢትዮጵያ በየትኛውም ዘመን የሌላውን ሀገር ሉዓላዊነት ደፍራ አታውቅም። የራሷንም ክልል ለሰኮንድም ቢሆን አስደፍራ አታውቅም።

ዛሬ ላይ ይህን ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሸጋገረ የጀግንነት አደራ ከከፍተኛ ወታደራዊ ቴክኖሎጂ ጋር በማዋሃድ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለሚዳፈሩ ጠላቶቿ ሁልጊዜም የማይተኛ ስጋት ሆኗል።

ጠላትን አስቀድሞ በማዳከምና የመግታት ቁመና ላይ በመድረስ፣ ጦርነትን ከማሸነፍ አልፎ ጦርነት እንዳይፈጠር የማስቀረት አቅም ገንብታለች።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከባህላዊው የምድርና የተራራ ላይ ውጊያ ሥልጠናዎች ባሻገር፣ አቅሙን ወደ አየርና ባሕር ኃይል በማሸጋገር በከፍተኛ ደረጃ መዘመን ችሏል።

በዘመናዊ ወታደራዊ ዕዝ፣ ቁጥጥር፣ ኮሙኒኬሽንና መረጃ አሰባሰብ ቴክኖሎጂዎችን ታጥቋል። በተለይም በድሮን ቴክኖሎጂ ትክክለኛ መረጃን የመሰብሰብ፣ በካሚካዜ አስወንጫፊዎች ደግሞ የጠላትን ምሽግ የመደርመስ እንዲሁም በልዩ ኃይሎቹ አማካኝነት ስትራቴጂያዊ ቦታዎችን በፍጥነት የማጥቃት ኃይል የመቆጣጠር አቅሙ የሠራዊቱን ወደር የለሽ ብቃት ያረጋግጣል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የመከላከያ ሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች በተደጋጋሚ እንደሚያስምሩበት፣ ይህ በቀጣናው ተወዳዳሪ የማይገኝለት ፕሮፌሽናል ተቋም እውነተኛ ክብሩ ያለው በውጊያ አቅሙ ብቻ ሳይሆን፣ አጥንቱን ከስክሶ፣ ደሙን አፍስሶ ሀገር የሚያቆም፣ ለምትጸናው ኢትዮጵያ የመጨረሻው የሉዓላዊነት ዋስትና መሆኑ ላይ ነው።

ከወታደራዊ ብቃቱ ባሻገር፣ ይህ ሠራዊት ከሕዝብ አብራክ የወጣና ሕዝብን ከማንኛውም አደጋ የሚታደግ እውነተኛ የሕዝብ ደጀን ነው። በሰላሙ ጊዜ ሰይፉን ወደ ማረሻ በመቀየር፣ በሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች፣ በግብርና ሥራዎችና በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሮች ላይ በግንባር ቀደምትነት የሚሳተፍ ንቁ የልማት ኃይል ጭምር መሆኑንም በተግባር አስመስክሯል።

ይህ ስትራቴጂያዊ እና ዘመናዊ የኃይል ግንባታ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅም ባለፈ በቀጣናው የኃይል ሚዛን ላይ ጉልህና አዎንታዊ ተጽዕኖ በማሳደር አካባቢያዊ የጸጥታ ዋልታ ሆኖ አገልግሏል።

ከሶማሌ እስከ ምጽዋ ጫፍ በባሕር ሊያጋጥሙ የሚችሉ ሽብሮችን በንቃት ከመከታተል አንስቶ በሱዳን፣ በአቢዬ እና በሶማሊያ አልሸባብን በመደምሰስ የተከናወኑት የሰላም ማስከበር ዘመቻዎች፣ የሠራዊታችንን ኃይል የማንጸባረቅ አቅም እና የአፍሪካ የነፃነት ቀንዲልነቱን በውል ያሳያሉ።

ዘመናዊ የጦር መሣሪያን ከኢትዮጵያዊ ጀግንነት፣ ከተጨባጭ ብቃትና ከብረት የጠነከረ ዲሲፕሊን ጋር ያዋሄደው ይህ ሠራዊት፣ ደሙን ገብሮ ሀገርን እያቆመ የሚገኝ የሕዝብ ኩራት ነው። የታሪክ አደራውን በመቀበል፣ በቀጣናው ሰላም፣ ልማት እና ብልጽግና እንዲረጋገጥ አህጉራዊ ኃላፊነቱን በከፍተኛ ደረጃ እየተወጣ የሚገኝ የዘመናችን መከታና የድል ሠራዊትም ጭምር ነው።

በበረከት ሽመልስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: