በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ በሕዝብ ቁጥር፣ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እና በጂኦፖለቲካዊ ተፅዕኖዋ ቀዳሚ ከሆኑ ሀገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ያሳየችው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለቀጣናው ትልቅ የእንቅስቃሴ ሞተር ሆኗል።
ሆኖም የሀገራችን ፈጣን የሕዝብ ቁጥር ዕድገት እና የኢንዱስትሪ መስፋፋት ከተጋረጡበት ትላልቅ ማነቆዎች አንዱ የባሕር በር አልባነት ጉዳይ ነው።
አሁን ላይ የሕዝብና የመንግሥት ዋና አጀንዳ ሆኖ የቀረበው ባሕር በር የማግኘት ፍላጎት፣ ከፖለቲካዊ ጥያቄነት ባለፈ ለሀገራችን የኢኮኖሚ ኅልውና እና ዘላቂ ዕድገት ወሳኝ መሠረት ነው።
ኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ንግዷን ለማከናወን በጎረቤት ሀገራት ላይ ጥገኛ በመሆኗ፣ በየዓመቱ ከ1.5 እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር ለወደብ ኪራይ፣ ለትራንስፖርት እና የመጋዘን አገልግሎት ታወጣለች። ይህም በኢኮኖሚዋ ላይ በርካታ ተፅዕኖዎችን እያሳደረ ይገኛል።
በየዓመቱ የሚከፈለው የውጭ ምንዛሪ ወጪ ለሀገራችን አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል። የወደብ አገልግሎት መዘግየቶች እና ከፍተኛ የወደብ ታሪፎች የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑም ያደርጋል።
ኢትዮጵያ ቀጥተኛ የባሕር በር ወይም የራሷ የወደብ አገልግሎት ማግኘቷ በኢኮኖሚዋ ላይ መሠረታዊ ለውጦች ያመጣል።
ከእነዚህም ውስጥ የራሷ የሆነ የባሕር በር ማግኘት ለወደብ ክፍያ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይቀንሳል። በዚህም የተቆጠበው ገንዘብ ለሌሎች መሠረታዊ የልማት ፕሮጀክቶች እንደ ትምህርት፣ ጤና እና መሠረተ ልማት እንዲውል ያስችላል።
ኢትዮጵያ በስፋት እየገነባቻቸው ያሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና የግብርና ምርቶች እንደ ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ አበቦች እና የእንስሳት ምርቶች ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ በፍጥነት እና በዝቅተኛ ወጪ እንዲደርሱ ያደርጋል። ይህም የወጪ ንግድ አቅሟን በእጥፍ ለማሳደግ ያስችላታል።
በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ከሚመዝኗቸው ዋና ዋና መስፈርቶች አንዱ የቀላልና እርካሽ የትራንስፖርት አገልግሎት መኖሩን ነው። አስተማማኝ የባሕር በር መኖርም ኢትዮጵያን ለውጭ ኢንቨስተሮች የበለጠ ማራኪ ያደርጋታል።
እንዲሁም የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት በጋራ የመልማት መርህ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በኃይል፣ በትራንስፖርት፣ በንግድና በቱሪዝም ዘርፎች ሰፊ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር መንገድ ይከፍታል።
የባሕር በር ፍላጎት የጸብ ወይም የውዝግብ መነሻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን የሕዝብ ቁጥርና የኢኮኖሚ አቅም ታሳቢ ያደረገ የኅልውና ጥያቄ ነው።
በቀጣናው ሰላምና ዘላቂ ልማት እንዲረጋገጥ የዲፕሎማሲያዊ እና የሕጋዊ መንገዶችን በመከተል፣ በጋራ ጥቅም እና በስምምነት ላይ የተመሠረተ ባሕር በር ማግኘት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሕዳሴ ከማፋጠኑም በላይ፣ ለአፍሪካ ቀንድ አጠቃላይ እድገትና መረጋጋት ትልቅ መሠረት ይጥላል።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: