የኢትዮጵያ ብልጽግና ዘላቂ የሚሆነው ዛሬ በምንጥለው ጠንካራ መሠረት ልክ ነው። እንደ ሀገር የጀመርነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ደግሞ የዚሁ ዘላቂ ብልጽግና ዋና አካልና የነገዋን ኢትዮጵያ ተስፋ የምንቀርጽበት ትልቅ ሀገራዊ ንቅናቄ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ለሚቀጥለው ትውልድ የብልጽግና መሠረት ከምንጥልባቸው መንገዶች አንዱ ዛፎችን መትከል ነው” በሚል የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን በተመለከተ ያስተላለፉት መልዕክት ይህን ያረጋግጣል።
ችግኝ ወይም ዛፍ መትከል የምድርን አየር ብክለት ማጽዳት አሊያም አካባቢን መንከባከብ ብቻ አይደለም፤ ከምንም በላይ ለወደፊቱ ትውልድ የሚተላለፍ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና አካባቢያዊ ኢንቨስትመንት ጭምር ነው።
በየዓመቱ የምንተክላቸው በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች ለአፈራችን ለምነት፣ ለውኃ ሀብታችን ደኅንነት እንዲሁም ለምግብ ዋስትናችን መረጋገጥ ቀጥተኛ አስተዋጽኦ አላቸው።
አፈር ሳይሸረሸር ሲቀር እና ወንዞች ሳይነጥፉ ሲፈሱ የግብርናው ዘርፍ ይበልጥ ይጠናከራል፤ ይህም በምግብ ራስን የመቻል አቅማችንን ያጎለብታል።
በተጨማሪም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ሀገራዊ አንድነትንና የጋራ ኃላፊነትን በተግባር ያሳየንበት አጋጣሚ ነው።
ከአረጋውያን እስከ ሕፃናት፣ ከአርሶና አርብቶ አደር እስከ ነጋዴ፣ ከተማሪ እስከ ምሁራን ያደረጉት ተሳትፎ ኢትዮጵያውያን ለጋራ ዓላማ በአንድ ላይ የመቆም አቅማቸውን አስመስክረዋል። ይህ ባህል ደግሞ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ ትልቅ የአስተሳሰብ ብልጽግና ነው።
ለቀጣዩ ትውልድ የምንተወው ትልቁ ውርስ የተቀደሰች፣ የተጠበቀችና በምግብ ራስዋን የቻለች ሀገርን ነው። ዛሬ የምንተክላት እያንዳንዷ ችግኝ ነገ ለልጆቻችን መጠለያ፣ የምግብ ምንጭና የኢኮኖሚ መሠረት ትሆናለች።
ስለሆነም አረንጓዴ ዐሻራችንን ማኖራችን የዕለት ተዕለት ተግባራችን እና ሀገራዊ ግዴታችን ሊሆን ይገባል።
ዛሬ አፈር ስንቆፍርና ችግኝ ስንተክል፣ ነገ ለሚመጣው ትውልድ የብልጽግናን መሠረት እያነጽን መሆናችንን አንዘንጋ። የአረንጓዴ ዐሻራችን ውጤት የነገዋ ኢትዮጵያ ውበትና ጥንካሬ ነው፡፡
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: