Search

በሰላም ብዕር የሚጻፍ ታሪክ፤ ልዩነትን በምክክር የመሻገር ጥበብ

ሓሙስ ሐምሌ 23, 2018 103

በሺዎች የሚቆጠሩ የበጎ ሃሳቦች እና የጋራ መግባቢያ ድልድዮች ባሉበት ሀገር ትኩረትን በጥርጣሬ እና በአሉታዊ ነገሮች ላይ ማድረግ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል።

ባለፉት ጊዜያት ከመልካም እሴቶች ይልቅ ጥቂት አሉታዊ ጉዳዮችን በመመንዘር ለፖለቲካ ፍጆታ እና ለራስ ጥቅም የመጠቀም አዝማሚያዎች በስፋት ተስተውለዋል።

ይህም በህብረተሰቡ ውስጥ መተማመን እንዲጠፋ የፖለቲካ ፉክክሮች በአዎንታዊ የሃሳብ ልዕልና ሳይሆን እርስ በርስ ሽኩቻ ላይ እንዲመሠረቱ እና ከሀገር ጥቅም ይልቅ ለቡድን ፍላጎት ማዘንበልን አስከትሏል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ የምትሻገረው በአሉታዊ ትርክት ሳይሆን በጋራ መከባበር በውይይት እና በአብሮነት ነው። ከከፋፋይ አስተሳሰቦች አዙሪት በመላቀቅ ችግሮችን በቅንነት እና በአዎንታዊ መነጽር ማየት መላው ዜጋ ሊያዳብረው የሚገባ ባህል ነው።

ፖለቲካ የንግድ ሥራ ሳይሆን የዜጎች የህልውና እና የዕድገት መሠረት በመሆኑ ከግል እና ከቡድን ጠባብ ፍላጎቶች በመላቀቅ ለጋራ ሀገር ቅድሚያ መስጠት የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ሀገርን የሚያጸናው ሰላም ፍቅር እና ምክክር እንጂ ጸብ እና ጦርነት ሀገርን ስለሚያሳንሱ እና ሕዝብን ለስቃይ ስለሚዳርጉ ነው።

ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው ታላቁ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የልዩነት ማነቆዎችን በውይይት ለመፍታት እና የጋራ ብሔራዊ ትርክት ለመገንባት ትልቅ እገዛ እያደረገ ይገኛል።

ሀገራዊ ምክክር በከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ወይም የሽግግር ወቅት በባለድርሻ አካላት መካከል ስምምነትን ለመፍጠር ዋና ዋና ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እና የአመጻ እንቅስቃሴዎችን ለማራቅ የሚያስችል በሀገር በቀል ባለቤትነት የሚመራ ልዩ የጋራ መገናኛ መንገድ ነው።

ሂደቱም ክርክሮችን ከተለመደው የፖለቲካ ልሂቃን ውሳኔ ሰጪነት አሻግሮ ከፖለቲካ የተገለሉ ወይም ዝቅተኛ ውክልና ያላቸው ወገኖችን በማሳተፍ አካታችነትን ያረጋግጣል።

ምክክሩ ማጥቃትን መከላከልን እና በአዋራጅ ግምቶች ላይ የተመሠረቱ ድምዳሜዎችን በማስወገድ በግልጽ የመነጋገር እና የመደማመጥ ባህልን ያጎለብታል።

ይህም በመንግሥት እና በህብረተሰቡ መካከል አዲስ የማህበራዊ ውል ለማሰር ሰብዓዊ ቀውሶችን ለማቃለል መዋቅራዊ ማስተካከያዎችን ለማድረግ እና ዘላቂ የሰላም ግንባታ ማዕቀፍ ለመገንባት ከፍተኛ መንገድ ይከፍታል።

በመሆኑም በቅንነት እና በጋራ መደማመጥ ላይ የተመሠረተው ይህ ሀገራዊ የምክክር ሂደት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለብዙዎች ትልቅ ተስፋን ፈጥሯል።

ኢትዮጵያውያን በአንድ ጣሪያ ሥር ተሰብስበው ችግሮቻቸውን በምክክር መፍታታቸው ውስጣዊ አንድነትን ነጻነትን እና ሉዓላዊነትን የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ ለነገዋ ሀገር የሰላም እና የፍቅር መሠረት በመጣል ለወደፊቱ ትውልድ በሰላም ብዕር እና ብራና የተጻፈ ኩሩ ታሪክ ለማስረከብ ያስችላል።

በብሌን ደምበሎ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: