Search

ባለፉት 5 ዓመታት ለትምህርት ጥራት መሠረት የሚጥሉ አበይት ተግባራት ተከናውነዋል፡- ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

ሓሙስ ሐምሌ 23, 2018 204

 

‎የትምህርት ሚኒስቴር አመራሮች እና ሠራተኞች በ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና በቀጣይ ዓመት እቅድ ላይ ውይይት አድርገዋል።

‎የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ ትምህርት የሀገር ዕድገትም ሆነ ውድቀት ነጸብራቅ በመሆኑ በትኩረት ሊሠራበት ይገባል።

‎ባለፉት 5 ዓመታት ለትምህርት ጥራት መሠረት የሚጥሉ ቁልፍና አበይት ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

‎ከተከናወኑ ውጤታማ ሥራዎች መካከልም የሥርዓተ ትምህርት ለውጥና የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት ማሻሻል በተለይም ደረጃቸውን የጠበቁ የቅድመ አንደኛ፣ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታና እድሳት ሥራ እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

‎የወደፊቱ መሪዎችና ሳይንቲስቶች የሚፈሩባቸው ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በሁሉም ክልሎች የመገንባት እና የማቋቋም ሥራ እየተሠራ መሆኑን ፕሮፌሰር ብርሃኑ አመላክተዋል።

‎የሁለተኛ ደረጃ መጻሕፍትን 1 ለ 1 ከማዳረስ በተጨማሪ ክልሎችን በመደገፍ የቅድመ አንደኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የመማሪያ መጽሐፍ በማሳተም ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

‎ባለፉት አምስት ዓመታት በተሠራው ሥራ ‎በትምህርት ቤት የተማሪዎች ምገባ አቅም 8.9 ሚሊዮን ማድረስ መቻሉን ገልጸው፣ በቀጣይ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

‎በ12ኛ ክፍል ፈተና ከኩረጃና ከስርቆት ነጻ እንዲሆን በ2016 የተጀመረውን የበይነ መረብ ፈተና በዚህ ዓመት ከ62 በመቶ በላይ ማድረስ መቻሉንና በቀጣይ ዓመት 100 ፐርሰንት ለማድረስ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

‎በከፍተኛ ትምህርት ረገድም የዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ቦርድና አመራሮች ከአካባቢያዊነት ነጻ በሆነ መንገድ በብቃትና በውድድር ላይ የተመሠረተ አኳኋን እንዲመረጡና እንዲመደቡ የሚያስችል ሥርዓት ተፈጥሮ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

‎ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በተልዕኮና ባላቸው ጸጋ መሠረት የመማር ማስተማር ምርምር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን እንዲሰጡ ሥርዓት ተበጅቶ ተግባራዊ መደረጉን ማብራራታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: