Search

የትግራይ ሕዝብ ሕወሓትን ሙሉ በሙሉ ነጥሎ ጥሎታል፡- አቶ አምዶም ገብረሥላሴ

ሓሙስ ሐምሌ 23, 2018 93

የትግራይ ሕዝብ ከየትኛውም ጊዜ በላይ በአሁኑ ወቅት ሕወሓትን ሙሉ በሙሉ ነጥሎ የጣለበትና ድርጅቱ ከፍተኛ የቅቡልነት ማጣት ያጋጠመው ወቅት ላይ እንደሚገኝ የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አምዶም ገብረሥላሴ ተናገሩ።

ሊቀመንበሩ አክለው እንዳመለከቱት ድርጅቱ የሚያወጣቸው መመሪያዎችና ትዕዛዞች በኅብረተሰቡ ዘንድ ምንም ዓይነት ተቀባይነት የሌላቸው ሲሆን፣ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ፓርቲው ወደ ሦስት በመከፋፈል በጥቅምና በዝምድና የተሳሰሩ ጥቂት ጄነራሎችንና ታጣቂዎችን ብቻ ያቀፈ አክራሪ የቤተሰብ ስብስብ ሆኖ ቀርቷል።

ህዝቡ ባለፈው ጦርነት ያተረፈው ነገር አለመኖሩን በማንሳት ተቃውሞውን ቢያሰማም፣ ድርጅቱ ከሌሎች ኃይሎች ጋር ጥምረት በመፍጠር መመሪያዎችን በማውጣት ወጣቱን በኃይል የመልመልና የማፈስ ድርጊት ውስጥ መግባቱን አቶ አምዶም ከኢቲቪ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጠቁመዋል።

አሁን ላይ ድርጅቱ ይህን ዓላማውን ለማስፈጸም ዋና ምንጩ አድርጎ የያዘው ከውጭ ኃይሎች የሚገኝን ድጋፍ መሆኑን ሊቀመንበሩ ጠቅሰዋል።

የፕሪቶሪያው ስምምነት ተፈናቃዮች እንዲመለሱና ሰላም እንዲሰፍን ያመጣውን ተስፋም ወደ ጎን በማለት ለተፈናቃዮች መመለስ እንቅፋት በመሆን እንደገና ወደ ስልጣን ለመምጣት ትኩረት ማድረጉን ገልጸዋል።

ሕወሓት በሚፈጥረው ጦርነት ያተረፈው ሞት፣ አካል መጉደልና መፈናቀል ብቻ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አምዶም፣ አሁን እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ሕዝባዊ ዓላማ ያለው ሳይሆን ከዚህ ቀደም የዘረፈውን ሀብት ለማስጠበቅና ከተጠያቂነት ለማምለጥ ጠመንጃን እንደ ከለላ የመጠቀም ሙከራ መሆኑን ገልጸዋል።

በድርጅቱ ምክንያት ያደረሰው የመከፋፈል አደጋ የፖለቲካ ኃይሉን ብቻ ሳይሆን ተከታዮቹን ጭምር ያካተተ መሆኑንም አቶ አምዶም አብራርተዋል።

በኢንቲሃድ አብራር

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: