Search

የአረንጓዴ ዐሻራ የምሥራች ፍሬዎች፦ ከምግብ ዋስትና እስከ ማክሮ ኢኮኖሚ ደጋፊነት

ዓርብ ሐምሌ 24, 2018 126

በኢትዮጵያ ታሪክ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን ማቀናጀት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ለዘመናት ፈታኝ ሆኖ ቆይቷል። የተፈጥሮ መዛባት ደግሞ የችግሩ ዋና መንሥኤ ነበር።

ይህንን የሥነ-ምኅዳር መዛባት ለመቀልበስ 2011 . የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የምሥራች ፍሬውን ማፍራት ጀምሯል።

እነዚህ የምሥራች ፍሬዎች ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለምግብ ዋስትና እና ለማክሮ ኢኮኖሚ ዕድገት ዋነኛ ደጋፊ ሆነዋል።

በመርሐ ግብሩ ከተተከሉት 48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መካከል አብዛኞቹ ሁለገብ ጠቀሜታ ያላቸው የግብርና-ደን (Agroforestry) እና የፍራፍሬ ዝርያዎች ናቸው። ይህ አካሄድ የአካባቢ ጥበቃን ዓላማ ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ጋር አዋህዶታል። የተተከሉት ፍራፍሬዎች ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፈው ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።

የአረንጓዴ ዐሻራ በሀገር ውስጥ የምግብ ዋስትና ላይ ያመጣው ለውጥ ጉልህ ነው። በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሲዳማ፣ በደቡብ፣ በደቡብ ምዕራብ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የተዘረጉ የፍራፍሬ ልማት ክላስተሮች የአርሶ አደሩን የአመጋገብ ሥርዓት ቀይረዋል።

በአፋር ክልል ከሚተከሉት ችግኞች ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት የፍራፍሬ ዝርያዎች መሆናቸው፣ በሞቃታማ አካባቢዎች ጭምር የምግብ አቅርቦት እንዲረጋገጥ አስችሏል። የተተከሉት ዛፎች የከርሰ ምድር ውኃን በማበልጸግ፣ የአፈር ለምነትን በማሻሻል እና ብዝኃ-ሕይወትን በማሳደግ ለስኬት መሰረት ጥለዋል።

ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባሻገር እነዚህ ምርቶች የኢትዮጵያን የኤክስፖርት ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ እየቀየሩት ነው። በመርሐ ግብሩ 8 ቢሊዮን በላይ የቡና ችግኞች በመተከላቸው ታሪካዊ የቡና ልማት ንቅናቄ ተፈጥሯል።

የሀገራችን የደን ሽፋን 17.2 በመቶ ወደ 23.6 በመቶ ከፍ ማለቱ ለቡና ተክሎች ተፈጥሯዊ ጥላ እና እርጥበት ፈጥሮላቸዋል። በዚህም የቡና ኤክስፖርት መጠን 2011 . ከነበረበት 246 ሺህ ቶን በከፍተኛ ደረጃ አድጎ፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 600 ሺህ ቶን ለውጭ ገበያ ቀርቦ 3.1 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማስገኘት ችሏል። ይህ ገቢ የተገኘው ከሚመረተው ቡና 50 በመቶው ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ውሎ ከቀረው 50 በመቶ ምርቱ ነው።

በአቮካዶ ልማትም ኢትዮጵያ ከቀዳሚዎቹ የአፍሪካ አምራች እና ላኪ ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ በቅታለች። በተለይም ሃስ (Hass) እና ኢቲንገር (Ettinger) በተባሉ የተሻሻሉ ዝርያዎች ላይ በተደረገው ትኩረት የአቮካዶ ኤክስፖርት በየዓመቱ 36.3 በመቶ ዕድገት እያሳየ ነው።

በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ብቻ ዘንድሮ 70 ሺህ ኩንታል አቮካዶ ለውጭ ገበያ የቀረበ ሲሆን፣ አርሶ አደሮችም ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በቀጥታ የገበያ ትሥሥር ፈጥረዋል።

ምርታችንን ከሐምሌ እስከ መስከረም ባለው ጊዜ ለዓለም ገበያ ማቅረባችን ደግሞ፣ በሌሎች አምራች ሀገራት (እንደ ፔሩ ባሉ) ምርት በሚያልቅበት ወቅት የሚፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም የተሻለ ተፈላጊነት እና ዋጋ እንድናገኝ አድርጎናል። ልማቱን ለማስፋፋትም በብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም 38.57 ቢሊዮን ብር ተመድቧል። 

ይህንን እያደገ የመጣ ምርት በዘመናዊ መንገድ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ከሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር የተናበቡ ሰፊ የሎጂስቲክስ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።

በሞጆ ደረቅ ወደብ 50 ሚሊዮን ዶላር ወጪ "Cool Port Addis" ቀዝቃዛ ማከማቻ በመገንባት ላይ ሲሆን፣ የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር መስመርን በመጠቀም ፍራፍሬዎችን በማቀዝቀዣ ኮንቴይነሮች ወደ ውጭ መላክ ተጀምሯል።

በተጨማሪም በሲዳማ ክልል የሚገኘው የይርጋለም አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ከአቮካዶ የምግብ እና የኮስሞቲክስ ዘይት በማምረት እሴት የተጨመረበት የኢንዱስትሪ ምርት ወደ ውጭ በመላክ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ ይገኛል።

በቀጣይም እንደ ማካዳሚያ እና ኮኮዋ ያሉ አዳዲስ ዝርያዎች በጥላ ሥር ሰብልነት መልማታቸው የኤክስፖርት አማራጫችንን ይበልጥ ያሰፋዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አርሶ አደሩ ዛፎችን ተንከባክቦ ቀጥታ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ የአስተሳሰብ ሽግግር ያመጣ ሰሆን፣ 1.2 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።

በዚህም መሠረት አረንጓዴ ዐሻራ ኢትዮጵያን ወደ ዘላቂ የማክሮ-ኢኮኖሚ ዕድገት እያሸጋገረ ያለ ብሔራዊ የልማት ማዕቀፍ ነው።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: