Search

ለኢትዮጵያ ስፖርት አዲስ ምዕራፍ የከፈተው አረንጓዴ ዐሻራ

ዓርብ ሐምሌ 24, 2018 110

 ኢትዮጵያ በአዲስ የለውጥ ጎዳና ውስጥ በምትጓዝበት በዚህ ዘመን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) የሚመራው መንግሥት በመደመር እሳቤ ላይ ተመሥርቶ ሀገራዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ ካከናወናቸው ታላላቅ እና ታሪካዊ ሥራዎች መካከልየአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርአንዱ እና ዋነኛው ነው።

ይህ ተግባር ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም ያማከለ ነው። የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ እና የአየር ንብረት ለውጥን ከመቋቋም ባሻገር፣ ለመጪው ትውልድ ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት በማቆየት የተሻለች ኢትዮጵያን የመገንባት ታላቅ ዐሻራ ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ የሕልውና አደጋ በሆነበት በዚህ ጊዜ፣ ኢትዮጵያ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ችግሩን ለመፍታት የሰጠችው ትኩረት ለቀጣዩ ትውልድ የምታስረክበው ሕይወት ሰጪ ውርስ ነው።

የመደመር መንግሥት አረንጓዴ ልማትን የሕልውና ጉዳይ አድርጎ በመውሰዱ፣ የብዝኃ ሕይወት እና የሥነ ምኅዳር መታደስን በከፍተኛ ሁኔታ አጠናክሯል።

በደረቁ እና በተራቆቱ ተራሮች ላይ የሚካሄዱት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሮች ተፈጥሮን በመታደግ የውኃ ሀብት እና ለም አፈር እንዲጠበቅ አድርገዋል።

ይህ የአረንጓዴ ልማት ከሌሎች ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በተጨማሪ፣ ከሀገራችን ስፖርት፤ በተለይም ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ስሟን በወርቅ እንድትጽፍ ካደረገው የአትሌቲክስ ዘርፍ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው።

ስፖርት እና ተፈጥሮ የማይነጣጠሉ የሕይወት ሐረጎች ናቸው። ስፖርተኛው በሜዳ ላይ ላብ ሲያፈስስ፣ የሚያስፈልገው መሠረታዊ ነገር ንጹሕ ኦክስጅን እና ምቹ የአየር ሁኔታ ነው።

በመሆኑም ይህ ለትውልድ የሚደረግ ታላቅ ኢንቨስትመንት በቀጥታ ጤናማ፣ አምራች እና ብቁ የስፖርት ትውልድን ለመፍጠር ጠንካራ መሠረት ይጥላል።

በስፖርት ሳይንስ ምሁራን እንደተረጋገጠው፣ በተለይም በረጅም ርቀት ውድድሮች የሳንባ አቅም እና የኦክስጅን ሥርጭት ለውጤታማነት ወሳኝ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው።

አትሌቶች ጠንካራ ልምምድ በሚያደርጉበት ወቅት ከወትሮው በእጥፍ የሚጠጋ ኦክስጅን ወደ ሳንባቸው ያስገባሉ። አየር በካርቦን እና በጥቃቅን ብናኞች ከተበከለ ደግሞ የአትሌቶች የሳንባ አቅም ይዳከማል።

አረንጓዴ አካባቢዎች የስታዲየሞችን እና የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ውበት ከመጨመር ባሻገር፣ የተፈጥሮ ጥላ እና ቅዝቃዜ በመፍጠር ለአትሌቶች፣ ለአሠልጣኞች እና ለተመልካቾች ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ።

ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ የምትታወቅበትን የረጅም ርቀት የበላይነት ያረጋገጠችው በተፈጥሮ ስጦታዋ እና በከፍታ ቦታዎች በሚደረጉ ልምምዶች ነው።

እንጦጦ፣ ሱሉልታ እና አርሲ በቆጂን የመሳሰሉ አረንጓዴ እና ተራራማ አካባቢዎች የአትሌቶቻችን ዋና የማሠልጠኛ ስፍራዎች ናቸው።

የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ እነዚህን ተፈጥሯዊ የማሠልጠኛ ስፍራዎች ከከተሞች መስፋፋት እና ከተፈጥሮ መናጋት በመጠበቅ የሀገራችን የአትሌቲክስ ክብር ሕልውናው ተጠብቆ እንዲቀጥል ያግዛል። መንግሥትም ለእነዚህ አካባቢዎች ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት ልዩ ትኩረት መስጠቱ ይህ ተፈጥሯዊ ጸጋ ለትውልድ እንዲተላለፍ አድርጓል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ እንደ አፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያሉ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ ሰፊ ጥረት እያደረገች ትገኛለች። በዚህ ረገድ አረንጓዴ እና ንጹሕ ስታዲየሞች፣ የልምምድ ማዕከላት እና ጤናማ የአካባቢ አየር ውድድሮችን ለማስተናገድ ወሳኝ መስፈርቶች ሆነዋል።

ዓለም አቀፍ እንግዶችን እና አትሌቶችን ይበልጥ የሚማርከው የከተሞች ጽዳት፣ የአየር ንጽሕና እና የአረንጓዴ ስፍራዎች መስፋፋት ነው። ንጹሕና አረንጓዴ አካባቢ መኖሩ ኢትዮጵያ የዓለም አትሌቶች መጥተው የሚያሠለጥኑባት እና የሚወዳደሩባት የስፖርት ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን ዕድል ይፈጥራል።

አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማቶች እና የከተማ አረንጓዴ ቦታዎች የስፖርት ቱሪዝምን ለማስፋፋት መሠረት እየጣሉ ነው።

ዓለም አቀፍ የስፖርት ሕክምና ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ በአረንጓዴ ስፍራዎች እና ከብክለት ነጻ በሆነ አካባቢ ልምምድ የሚያደርጉ አትሌቶች የደም ዝውውራቸው የተሻለ፣ የልብ ምታቸው ጤናማ እና ከልምምድ በኋላ የማገገም ፍጥነታቸው ከፍተኛ ነው።

በመሆኑም መንግሥት ለአረንጓዴ ልማት የሰጠው ትኩረት በቀላሉ ዛፍ የመትከል ሥራ ብቻ ሳይሆን፣ የሀገርን የወደፊት ዕድገት የመቅረጽ፣ የትውልድን ጤና የማረጋገጥ እና የስፖርቱን ዘርፍ በጠንካራ መሠረት ላይ የመገንባት ስትራቴጂያዊ እርምጃ መሆኑን ያሳያል።

ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ያላትን ዓለም አቀፍ ገጽታ ለማስቀጠል እና ወደፊትም ትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ በምታደርገው ጉዞ፣ የአረንጓዴ ልማት ምቹ፣ ንጹሕና አስተማማኝ አካባቢን ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።

ዛሬ የምንተክላቸው የተስፋ ችግኞች ነገ ለሚያብቡት ስፖርተኞቻችን ንጹሕ አየርን፣ ለሀገራችን ስፖርት ዘላቂ ዕድገትን፣ ለመጪው ትውልድ ደግሞ ኩራት እና ሕያው ሀብትን የሚያስተላልፉ የአረንጓዴ ዐሻራዎች ናቸው።

በአዲስ የሺዋስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: