በኢትዮጵያ በሳይንስ፣ በመንግሥት አስተዳደር እና በዲፕሎማሲው ዘርፍ የላቀ ስኬት በማስመዝገብ ለሀገራቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱት አምባሳደር ስንቅነሽ እጅጉ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በ69 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ተለይተዋል።
የአምባሳደር ስንቅነሽ እጅጉ የትምህርት እና የሥራ ሕይወት ታሪክ በአጭሩ
በመጋቢት ወር 1948 ዓ.ም በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ከተማ የተወለዱት አምባሳደር ስንቅነሽ፤ በልጅነት ዘመናቸው በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ተዘዋውረው ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ1972 ዓ.ም በኬሚስትሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ እንዲሁም የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአናሊቲካል ኬሚስትሪ ከእንግሊዙ ኢስት አንግሊያ ዩኒቨርሲቲ በ1980 ዓ.ም አግኝተዋል።
በኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ በተለያዩ የኃላፊነት እርከኖች ሴቶችን ወክለው በላቀ አመራር አገልግለዋል፡፡ በ1990 ዓ.ም የማዕድን እና ኢነርጂ ምክትል ሚኒስትር፣ በ1994 ዓ.ም የማዕድን እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ፣ እንዲሁም በ2002 ዓ.ም የማዕድን ሚኒስትር በመሆን ሀገራቸውን በከፍተኛ ታማኝነት አገልግለዋል።
በማዕድን እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ቆይታቸው የኢትዮጵያን የማዕድን ሀብት ልማት ከማጠናከር ባሻገር፤ በጊቤ 1 እና 2፣ ጢስ ዓባይ 1 እና 2፣ ተከዜ፣ ፊንጫ አመርቲነሼ እና ጣና በለስ የኃይል ማመንጫዎች ግንባታ ጉልህ አሻራ አሳርፈዋል።
በተለይም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጥናት ተጠናቅቆ ወደ ግንባታ እንዲገባ እና በመጀመሪያዎቹ ዓመታት የግንባታ ክትትል ላይ የማይተካ ሚና ተጫውተዋል።
ከ2006 እስከ 2010 ዓ.ም በብራዚል፣ አርጀንቲና እና ቺሊ የኢትዮጵያ ልዩ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር በመሆን የሀገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም አስጠብቀዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባልነት (የቪዥን 2025 ዕቅድን በማርቀቅ)፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን፣ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በሌሎችም በርካታ ሀገራዊ ተቋማት ላይ በቦርድ ሰብሳቢነት እና አባልነት በብቃት መርተዋል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆንም አገልግለዋል።
በሳይንስ፣ በምህንድስና፣ በመንግሥት አስተዳደር እና በዲፕሎማሲ ዘርፍ ለሚሠሩ ወጣቶች በተለይም ለሴቶች ትልቅ ተምሳሌት የነበሩት አምባሳደር ስንቅነሽ፤ የሁለት ልጆች እና የአንድ የልጅ ልጅ እናት ነበሩ።
የአምባሳደር ስንቅነሽ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ነገ በአዲስ አበባ ገርጂ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ከቀኑ 6 ሰዓት ላይ እንደሚፈጸም ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢቢሲ በላከው መግለጫ ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ለአምባሳደር ስንቅነሽ እጅጉ ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች እንዲሁም የሥራ አጋሮች መ ጽናናትን ይመኛል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: