Search

የኢትዮጵያ ልብ፣ የጸና ዐለት!

ዓርብ ሐምሌ 24, 2018 98

ማንኛውም ግዙፍ አካል ሕያው ሆኖ የሚኖረው፣ ደሙን አዘዋውሮ የሚያቆመው ጤናማ እና ጠንካራ ልብ ሲኖረው ነው።

ለታላቂቱ ኢትዮጵያም የሕልውናዋ፣ የጽናቷ እና የክብሯ የልብ ትርታ የፀጥታ እና ደኅንነት ተቋሞቿ ናቸው።

ዛሬ ላይ በጥልቅ ሪፎርም ታድሰው፣ ለሀገራቸው ባላቸው ጥልቅ ፍቅር እና ወደር የለሽ የጽናት ቁርጠኝነት የተዋቀሩት እነዚህ ተቋማት፣ በእውነትም የማይነቃነቀው "የኢትዮጵያ ልብ" ሆነዋል።

እነዚህ ተቋማት የተጓዙበት የሪፎርም ሒደት፣ የሰው ኃይልን ከመጠናከር እጅግ ዘመናዊ የሆነ ተቋማዊ አቅምን፣ ሳይንሳዊ አሠራርን እና የላቀ ብሔራዊ ስሜትን መሠረት ያደረገ ነው።

ተቋማቱ የሉዓላዊነት የማይናወጥ ዐለት ሆነው የቆሙት በጽኑ እምነት፣ በቴክኖሎጂ ልዕልና እና በሕዝባዊነት ተገምደው ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገራችን የብረት ጋሻ እና የክብር አክሊል ነው። ሠራዊቱ ባለፉት የሪፎርም ዓመታት ከባህላዊ የውጊያ አቅም ተሻግሮ፣ ዓለም አቀፍ ስታንዳርዱን በጠበቀ የቴክኖሎጂ ልዕልና፣ በሰው አልባ አውሮፕላኖች (UAVs) እና በተራቀቀ የጦር ስትራቴጂ የታጠቀ አስፈሪ ኃይል ሆኗል።

 

ይሁን እንጂ የዚህ ሠራዊት ታላቁ ጉልበት የጦር መሣሪያው ብዛት ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያ ያለው የማያወላውል ጥልቅ ፍቅር እና አጥንቱን ከስክሶ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ያለው የጽናት ቁርጠኝነት ነው።

መከላከያ ሀገርን በክብር አስቀጥሎ፣ የውጊያ አቅሙን ጦርነትን ቀድሞ ወደ ማስቀረት አሸጋግሮ፣ ራሱን በዕውቀት እና በዲሲፕሊን ያነጸ የኢትዮጵያ ሕያው ጀግና ነው።

በሌላ ገጽ ደግሞ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ሳይታይ የሚያይ፣ ሳይሰማ የሚሰማ የሀገር ንቁ ዐይን ሆኗል። ተቋሙ ከሪፎርሙ በፊት ከነበረው የፖለቲካ ማፈኛ ታሪክ ሙሉ በሙሉ ተላቅቆ፣ ዛሬ የዜጎች ደኅንነት ዘብ እና የሀገር ሉዓላዊነት ጠባቂ ወደሆነ እጅግ ዘመናዊ የመረጃ ትንተና ተቋምነት ተሸጋግሯል። ይህ የተቋማዊ አቅም ግንባታ ሒደት፣ ሀገር ላይ የተቃጡ የጥፋት ሴራዎችን ገና በፅንሳቸው በማክሸፍ ኢትዮጵያ ሳትደናቀፍ የልማት ጎዳናዋን እንድትገፋ አስችሏታል።

ይህ ተቋም ለኢትዮጵያ ያለው ውድ ፍቅር የሚገለጸው ከእንቅልፍ በጸዳ 24 ሰዓት ተጠንቅቆ በመጠበቅ እና አደጋን ቀድሞ በመከላከል ሳይንሳዊ ጥበቡ ነው።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በተራው የሀገር ውስጥ ሰላም እና የሕግ የበላይነት የማይነቃነቅ ምሰሶ ነው። በሪፎርሙ ማግስት ማኅበረሰብን ያሳተፈ የቅድመ መከላከል አሠራርን ዘርግቶ፣ ዜጎችን በክብር የሚያገለግል እና የወንጀል ስጋቶችን በቴክኖሎጂ ታግዞ የሚያከሽፍ ዘመናዊ አቅም ገንብቷል።

የፌዴራል ፖሊስ አባላት በየመንገዱ፣ በየከተማው እና በየሀገራችን ማዕዘናት ውድ ሕይወታቸውን ገብረው የዜጎችን በሰላም ውሎ ማደር ሲያረጋግጡ፣ ከምንም በላይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያላቸውን የማይነጥፍ ፍቅር እና ታማኝነት በተግባር ያሳያሉ።

በአጠቃላይ፣ መከላከያ፣ ደኅንነት እና ፌዴራል ፖሊስ እያንዳንዳቸው የየራሳቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ በከፍተኛ የፕሮፌሽናል ብቃት እና ሥነ ልቦናዊ ልዕልና እየተወጡ፣ በአንድነት ግን የኢትዮጵያን ጽናት ያረጋገጡት "የኢትዮጵያ ልብ" ናቸው።

እነዚህ ተቋማት ፈተናዎች በበዙ ቁጥር እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትነው የነጠሩ፣ ለሕገ መንግሥቱ እና ለሕዝቡ ብቻ የታመኑ የሰላም ዋልታዎች ናቸው።

ማንም ደፍሮ እንዳይነካን፣ ማንም ኢትዮጵያን ዝቅ እንዳያደርጋት የገነቡት የተዋሐደ ተቋማዊ አቅም፣ የዛሬዋን ብቻ ሳይሆን የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያ ሕልውና አስተማማኝ ያደረገ ነው።

ዛሬም፣ ነገም፣ የኢትዮጵያ ልብ በነዚህ ጀግኖች ልጆቿ ደረት ውስጥ በጽናት፣ በክብርና በፍቅር ይመታል!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: