በዘመናዊው የጂኦ-ፖለቲካ እና የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ የአንድ ሀገር የባሕር በር ባለቤትነት የሀገርን ፖለቲካዊ ነፃነት፣ የዲጂታል ደኅንነትን፣ የዜጎችን ዕለታዊ ኑሮ እና የሕይወት አድን መድኃኒቶች አቅርቦትን የሚወስን የሕልውና እና የደኅንነት መሠረት ነዉ፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሕዝብ ብዛቷ 10ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ታላቅ ሀገር ብትሆንም፣ የባሕር በር አልባ ሆና እንድትቀጥል መደረጉ ሀገራችንን ዘመናትን ለተሻገረ ዘለቄታዊ የብሔራዊ ደኅንነት እና የኢኮኖሚ ማነቆ ዳርጓታል።
በዘመናዊው ዓለም የሀገር ምስጢር፣ የመረጃ ደኅንነት እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ከባሕር በር እና በውቅያኖስ ሥር ከሚዘረጉ የፋይበር ኦፕቲክስ መስመሮች ጋር በቀጥታ የተሳሰሩ ናቸው።
የባሕር በር የሌላት ሀገር የመረጃ አውታሯ፣ የዲጂታል ክላውድ ኢንክሪፕሽን አቅሟ እና ሳተላይቶቿ በሌሎች ሀገራት ግዛት ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ ስለሚገደዱ የዲጂታል እና የዳታ ገመናዋን ሙሉ በሙሉ ማስከበር አትችልም።
ከዲጂታል ደኅንነቱ ባሻገር ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ስትራቴጂካዊ ቁሳቁሶች እንዲሁም ወደ ውጭ የሚላኩ የሀገር ሀብቶች እንቅስቃሴ በሙሉ በሌሎች ሀገራት እጅ ሥር በመውደቁ፣ ሀገሪቱ በጂኦ-ፖለቲካዊ ፉክክር ውስጥ እንቅስቃሴዎቿ በቀላሉ እንዲከሸፉ እና ለተለያዩ የደኅንነት ሥጋቶች እንድትጋለጥ ያደርጋታል።
ይህ የደኅንነት ሥጋት በዜጎች ዕለታዊ ሕይወት እና የኢኮኖሚ ነጻነት ላይ የሚያሳድረው ጫና ደግሞ እጅግ ከባድ ነው። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ከባሕር በር ባለቤቶች ጋር ሲነጻጸሩ በሎጂስቲክስ እና ትራንስፖርት ላይ ከ50 እስከ 100 በመቶ የሚደርስ ተጨማሪ ወጪ ያወጣሉ።
ለምሳሌ ያህል አንድ ምርት ከቻይና ተጭኖ በጎረቤት ኬንያ ናይሮቢ ገበያ የሚሸጥበት ዋጋ እና ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ የሚሸጥበት ዋጋ ሲነጻጸር፣ በኢትዮጵያ ገበያ ላይ በሎጂስቲክስ ወጪ ምክንያት ብቻ ቢያንስ የ30 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ይታይበታል። ይህ ማለት አንድ ዜጋ የሚገዛው አልባሳት፣ ምግብ፣ ዘይት፣ ስኳር እና የግንባታ ግብዓት በሙሉ የባሕር በር አልባነት ያስከተለውን የዋጋ ንረት ታቅፎ የሚቀርብበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
የችግሩ አሳሳቢነት በይበልጥ ጎልቶ የሚታየው ደግሞ በዜጎች ጤና እና የሕይወት አድን መድኃኒቶች አቅርቦት ላይ ነው።
ኢትዮጵያ የመድኃኒትና የሕክምና መሣሪያዎች ፍላጎቷን ለማሟላት ከውጭ ሀገራት የምታስገባ በመሆኗ፣ በወደብ አገልግሎት መዘግየት እና በትራንስፖርት ታሪፍ ምክንያት የመድኃኒቶች ዋጋ ከፍ ይላል።
ከዚህም በላይ ጥብቅ የሙቀት ቁጥጥር የሚሹ ክትባቶች እና መድኃኒቶች በወደብ ላይ በሚፈጠር የመጓተት ሒደት እና በየብስ ትራንስፖርት ለረጅም ጊዜ በመቆየታቸው ምክንያት የአገልግሎት ዘመናቸው ሊቃረብ ይችላል።
የራስ የባሕር በር አማራጭ መኖር ግን የትራንስፖርት ወጪን እስከ 20 በመቶ በመቀነስ በችርቻሮ ገበያ ላይ የመድኃኒት ዋጋ እስከ 25 በመቶ እንዲቀንስ ከማድረጉም በላይ፣ የመድኃኒት አቅርቦቱን በጊዜ ተደራሽ በማድረግ የሺዎችን ሕይወት ለመታደግ ያስችላል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ዜጎቿን በበቂ መግቧ ራሷን ችላ በዓለም ተወዳድራ የላቀች ሀገር ለመሆን ካሉብን ዋነኛ ማነቆዎች ትልቁ ችግር የወደብ አልባነት ነው፡፡
የባሕር በር አጥቶ መቀጠል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ለቀይ ባሕር እና ለአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላም እና መረጋጋትም አዋጭ አለመሆኑንም ገልጸዋል።
ከምፅዋ ዳርቻ እስከ ሞቃዲሾ ጫፍ ድረስ ያለው 5 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሰፊና ለሁሉም የሚበቃ የባሕር ሀብት እያለ በጋራ አለመጠቀም አካባቢውን ለግጭት ዳርጎታል ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ትላልቅ ሀገራት ከቀይ ባሕር እና ኤደን ባሕረ ሰላጤ ጥበቃ መራቃቸው ደግሞ የዓለም ንግድ መስመርን ለአደጋ አጋልጧል።
ስለሆነም ሀገራችን የባሕር በር ባለቤት ካልሆነች ዘላቂ ብልፅግናን ማረጋገጥ አይቻልም። የባሕር በር ጥያቄ የአንድ አካል ወይም መንግሥት ጉዳይ ሳይሆን የውስጥ የፖለቲካ ልዩነቶችን የሚሻገር የትውልድ እና የሕዝብ የጋራ አጀንዳ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ አሁን ጥያቄውን ለዓለም ከማስረዳት አልፋ፣ እንዴት ይመለሳል ወደሚለው ተግባራዊ ምዕራፍ ተሸጋግራለች።
የባሕር በር የማግኘት አቅጣጫ የቅንጦት ሳይሆን የሀገርን ነፃነት የመጠበቅ፣ የዲጂታል ደኅንነትን የማረጋገጥ፣ የዜጎችን የመግዛት አቅም የማሳደግ እና የሕይወት አድን መድኃኒቶች አቅርቦትን የማረጋገጥ የሕልውና ጉዳይ ነው።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: