Search

ከ704 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ

ዓርብ ሐምሌ 24, 2018 87

 

የጉምሩክ ኮሚሽን ከሐምሌ 16 እስከ ሐምሌ 22 ቀን 2018  . ባደረገው ክትትል 661.1 ሚሊዮን ብር የገቢ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች እና 43.3  ሚሊዮን ብር የወጭ፤ በድምሩ 704.4 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በተለያዩ  ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች መያዛቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።

ከተያዙት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መካከል አዳዲስ እና ልባሽ ጨርቆች፣  ኤሌክትሮኒክስ፣  የግንባታ ዕቃዎች፣ ቡና፣ ጥራጥሬ፣  የተሽከርካሪ መለዋወጫ፣ የቁም እንስሳት፣ የመዋቢያ ዕቃዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ ዕፆች፣ መድኃኒት፣ ማዕድናት እና የውጭ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል።

በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ የገቢ እና የወጭ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር  አዋሽ፣  አዲስ አበባ ኤርፖርት እና ጅግጅጋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ /ቤቶች ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዙ በቅደም ተከተላቸውም 261 ሚሊዮን፣ 111 ሚሊዮን እና 90 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን መያዝ ችለዋል።

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላት እና ኅብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በጥቆማ እና በበረራ የተያዙ ሲሆን የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 34 ተጠርጣሪዎች እና 14 ተሽከርካሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የጉምሩክ ኮሚሽን በዚህ የሕግ ማስከበር ሥራ ላይ ለተሳተፉ የኮሚሽኑ ሠራተኞች እና አመራሮች፣ የክልል እና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ለመላው ሕዝብ ምስጋናውን አድርሷል።

የኮንትሮባንድ እና ሕገ ወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታት እና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመከላከል ጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባላድርሻ አካላት እና ኅብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የጉምሩክ ኮሚሽን ጥሪውን አቅርቧል።

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: