Search

"ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ያስመዘገቡትን ታሪካዊ የአንድነት ድል በሀገራዊ ምክክሩ ሊደግሙት ይገባል"፦ ተመካካሪዎች

ዓርብ ሐምሌ 24, 2018 49

በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ በመሳተፍ ላይ የሚገኙ ተመካካሪዎች፣ ኢትዮጵያውያን ያለ ልዩነት በአንድነት በመቆም በዓድዋ ያስመዘገቡትን ታሪካዊ ድል፣ አሁን ባለው የምክክር መድረክ ሀገራዊ መግባባትን በመፍጠር ሊደግሙት እንደሚገባ ገለጹ።

በምክክሩ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ አትሌቶችን ወክለው በመሳተፍ ላይ የሚገኙት መቶ አለቃ አትሌት በላይነህ ዴንሳሞ እንደገለጹት፣ አባቶች በዓድዋ ድል የተቀናጁት ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው እና ሀገርን በማስቀደም ነው።

አሁንም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ መላው ኢትዮጵያውያን በተወካዮቻቸው አማካኝነት ያለ ልዩነት እየመከሩ በመሆናቸው፣ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ሰላም እና ሀገራዊ መግባባትን ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከእንግሊዝ የመጡትን ዳያስፖራዎች ወክለው የተሳተፉት አቶ አለባቸው ደሳለኝ በበኩላቸው፣ በምክክሩ አትሌቱ፣ አርሶ አደሩ፣ ነጋዴው እና ምሁራንን ጨምሮ የሁሉም ሙያ እና የማኅበረሰብ ክፍሎች መወከላቸው፣ ሀገራዊ መግባባት፣ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋትን ለመፍጠር ትልቅ ዕድል ይዞ መምጣቱን ጠቁመዋል።

የትግራይ ክልልን በመወከል በምክክሩ ላይ የሚገኙት አቶ ሙሉጌታ ኃይለ ጊዮርጊስ በበኩላቸው፣ የቀደመው ትውልድ ወራሪን በአንድነት ድል እንዳደረገ ሁሉ፣ የዚህ ዘመን ትውልድ ደግሞ በምክክር አሠራር ጠባብ ብሔርተኝነትን እና ልዩነቶችን ድል ሊነሳ እንደሚገባ ገልጸዋል።

አክለውም የትግራይ ሕዝብ የሚሻው ሰላምን በመሆኑ፣ ልዩነትን በኃይል ለመፍታት የሚጥሩ አካላት ሁሉ ወደ ምክክሩ በመምጣት ለሀገር ሰላም ድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

በመስከረም ቸርነት

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: