Search

ከዛሬው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መግለጫ የተወሰዱ ዋና ዋና መልዕክቶች፡-

ዓርብ ሐምሌ 24, 2018 108

የምክክር እና የውይይት ሂደቱ

የቡድን ውይይቶች ማጠቃለያ፡- 250 አባላት ያሏቸው 16 ቡድኖች ላለፉት ሁለት ቀናት ያደረጉትን የጋራ ውይይት አጠናቅቀዋል። የተወያዩባቸውን እና የተቀራረቡባቸውን ሐሳቦች የያዘ ቃለ-ጉባኤ በማንበብ እና በመፈረም ለዋናው ጉባኤ ለማቅረብ ተዘጋጅተዋል።

የዋናው ጉባኤ ጅማሮ፡- በቀጣዩ ሰኞ ከጠዋቱ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በኋላ፣ 500 አባላትን የያዙ 8 ትልልቅ ጉባኤዎች ይጀመራሉ። ይህ ጉባኤም ሰፊ እና ወደ ተሻለ መግባባት የሚያመራ ውይይት ያደርጋል።

የተወካዮች ነጻ ምርጫ

የተወካዮች መረጣ፡- 12 ክልሎች፣ 2 የከተማ መስተዳድሮች እና ከፌዴራል ተቋማት የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሃይማኖት ተቋማት ወደ 330 የሚጠጉ ተወካዮቻቸውን መርጠዋል።

የኮሚሽኑ ገለልተኝነት፡- ተሳታፊዎቹ ተወካዮቻቸውን የመረጡት ኮሚሽኑ ባስቀመጠው መስፈርት መሠረት በራሳቸው ፍላጎት እና ውይይት ሲሆን፣ ኮሚሽኑ በምርጫው ሂደት ጣልቃ አልገባም።

መግባባት ላይ የመድረስ ሥርዓት

የመግባባት መለኪያ፡- በውይይቶቹ ቢያንስ እስከ 75 በመቶ የሚጠጋ መግባባት ላይ እንዲደረስ ይጠበቃል።

የልዩነቶች አፈታት፡- ሙሉ ስምምነት በማይደረስባቸው ጉዳዮች ላይ ክልሎች ወይም የተለያዩ አካላት ጥያቄ ካነሡ፣ ይህንን የሚፈታ የክልል እና የፌዴራል ተወካዮችን ያካተተ ትልቅ ቡድን ተዘጋጅቷል።

የተሳታፊዎች ቁርጠኝነት፡- ተሳታፊዎች ፅንፈኛ ሐሳቦችን ትተው ሀገርን በማስቀደም ወደ መሐል እየመጡ ነው። "የእኔ ብሔር/ማንነት" ትርክት ይልቅ "በጋራ እንሰማ" "የጋራ ማንነታችን እና መብታችን ይከበር" ወደሚል የጋራ መግባባት እየተሸጋገሩ ነው።

የባለሙያዎች ድጋፍ

በትልቁ ጉባኤ ውይይት ወቅት እንደ ሕገ-መንግሥት፣ መሬት ይዞታ፣ ፌዴራሊዝም እና የከተሞች አስተዳደር በመሳሰሉት አጀንዳዎች ላይ የተሳታፊዎች ጥያቄ ሲኖር፣ ከፍተኛ ባለሙያዎች ትክክለኛ የእውቀት ግብዓት (ማብራሪያ) ይሰጣሉ። ይህ የሚደረገው የተሳታፊዎችን አቋም ለማስቀየር ሳይሆን እውነታውን ለማስገንዘብ ነው።

የሕዝብ ተስፋ እና የሚዲያ ሚና

የሕዝቡ ተስፋ፡- ሕዝቡ በምክክሩ ላይ ያለው ተስፋ ሰላም፣ የመብት መከበር እና ለዘመናት የቆዩ የጭቅጭቅ አጀንዳዎችን በውይይት መፍታት ነው።

ሚዲያ እና ሐሰተኛ መረጃ፡- የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ትክክለኛ መረጃ በማሰራጨት ሐሰተኛ መረጃዎችን በመመከት እያደረጉት ላለው አስተዋጽኦ ኮሚሽነሩ ምስጋና አቅርበዋል። እውነታው ለሕዝብ በቀረበ ቁጥር የተሳሳቱ ትርክቶች እንደሚረቱ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: