ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር እና በአፍሪካ ቀንድ ስትራቴጂያዊ ቦታ ላይ ብትገኝም፣ በታሪክ አጋጣሚዎች የባሕር ላይ አቅሟን በየወቅቱ ስታጣ እና ስታገኝ ቆይታለች።
የኢትዮጵያ የባሕር ላይ ወታደራዊ እና የንግድ ታሪክ የሚጀምረው በጥንታዊው የአክሱም ሥልጣኔ ዘመን ነው። አክሱም በአዱሊስ ወደብ በኩል ለዓለም አቀፍ የንግድ መስመር ቁልፍ ማዕከል ነበረች።
በዚህ ታሪክ ውስጥ እጅግ ጎልቶ የሚነሣው በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አፄ ካሌብ በየመን ያደረጉት ታላቅ ዘመቻ ነው።
ከ70 በላይ የጦር መርከቦችን በማዘጋጀት 120 ሺህ የሚገመት ጦር በባሕር ላይ በማሻገር የተቀዳጁት ድል፣ ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ኃይሏን ከየብስ አልፋ በባሕር ላይ የማንጸባረቅ (Naval Power Projection) ከፍተኛ አቅም እንደነበራት በተግባር ያረጋገጠ ነው።
ከዘመናት መቋረጥ በኋላ፣ በ1950 እ.አ.አ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ስትቀላቀል፣ ሀገራችን የቀይ ባሕር ጠረፏን ዳግም አገኘች። ይህን ተከትሎ አፄ ኃይለ ሥላሴ በ1947 ዓ.ም ዘመናዊውን "የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ባሕር ኃይል" በይፋ መሠረቱ።
በምጽዋ ዋና ማዘዣውን ያደረገው ይህ ኃይል፣ በአስመራ ከተማ የባሕር ኃይል መኮንኖች ኮሌጅ (Naval College) በማቋቋም በባሕር ኃይል ሳይንስ የዲግሪ ትምህርት መስጠት ጀመረ።
በሪር አድሚራል እስክንድር ደስታ አመራር፣ እንዲሁም በውጭ ሀገራት መኮንኖች አማካሪነት ተቋሙ በአፍሪካ ቀንድ እጅግ የተከበረ ኃይል ለመሆንም በቃ። "ዘርአይ ድረስ (PC-1616)" እና "ኢትዮጵያ A-01" የተሰኙት ዘመናዊ መርከቦቻችን የብሔራዊ ኩራት ምልክቶች ነበሩ።
በ1966 ዓ.ም የተከሰተውን አብዮት ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ የጂኦፖለቲካዊ አቅጣጫ ወደ ምሥራቁ ዓለም በማዘንበሉ፣ ባሕር ኃይሉም ከፍተኛ የትጥቅ ለውጥ አደረገ። በዳህላክ ደሴቶች (ኖክራ) የሶቭየት የሎጂስቲክስ ማዕከል መቋቋሙን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ ዘመናዊ የሆኑ ሚሳይል እና ቶርፔዶ ተሸካሚ መርከቦችን ታጠቀች። በአፍሪካ ቀንድ ዘመናዊ የነበረው ይህ ኃይል የሠራተኛው ቁጥር 11 ሺህ 500 ቢደርስም፣ በኋላ ላይ የገጠመው የጥገና እጦት እና የውስጥ ጦርነት ሕልውናውን ፈተና ውስጥ ከተተው።
የክህደት፣ የቸልተኝነት እና የመበተን ጨለማ ዘመን
በ1983 ዓ.ም የደርግ መንግሥት መውደቅን ተከትሎ የሽግግር መንግሥቱ በፈጸመው ድርጊት ትውልድ የማይዘነጋው በባሕር ኃይሉ ላይ የተፈጸመ ታሪካዊ ክህደት ነበር። ኤርትራ ያለምንም የባሕር በር ድርድር እንድትገነጠል ሲፈቀድ፣ ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ሙሉ በሙሉ አጣች።
መነሻ ወደባቸውን ያጡት የኢትዮጵያ የጦር መርከቦች መንግሥት እንደ አላስፈላጊ ሸክም ቆጥሮ በመተው፣ በቀይ ባሕር ላይ ለመንከራተት ተገደዱ። በየመን ተጠልለው የነበሩ መርከቦች ከወደብ ሲባረሩ፣ ታሪካዊቷ የልምምድ መርከብ "ኢትዮጵያ (A-01)" ለቆሻሻ ብረትነት ተሸጠች።
በመጨረሻም ወደ ጅቡቲ ያቀኑት ቀሪ መርከቦች የወደብ ኪራይ ባለመከፈሉ በ1988 ዓ.ም በሐራጅ ተሸጠው ታላቁ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በይፋ ፈረሰ።
በክብር የተመለሰው ባሕር ኃይል፦ ዳግም ትንሣኤ
በክህደት ከፈረሰ ከ30 ዓመታት በኋላ፣ "ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ሀገር ያለ ባሕር በር መኖር አትችልም" በሚል የሪፎርም እሳቤ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሕር ኃይሉ ዳግም በአዲስ መልክ እንዲቋቋም አደረጉ።
ከፈረንሳይ እና ሌሎች አጋር ሀገራት በተገኘው ስምምነት አቅሙን የገነባው ይህ አዲስ ኃይል፣ በቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ አዛዥነት እየተመራ ይገኛል።
ዋና ማዘዣ ጣቢያዎቹን በአዲስ አበባ እና ባሕር ዳር በማድረግ፣ በቢሾፍቱ (ባቦጋያ) እና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ (EMTI) ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የማሪን ኮማንዶ እና የባሕረኝነት አካዳሚዎችን አቋቁሞ ምርጥ የሰው ኃይል ያለው አስፈሪ የባሕር ኃይል ተገንብቷል።
የስትራቴጂያዊ የኢኮኖሚ ጥበቃ እና የወደፊት አቅጣጫ
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ዳግም መቋቋም በታሪካዊ ስሜታዊነት ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ የጂኦፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ደኅንነት ስሌት ላይ የተመሠረተ ነው።
ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር የመመለስ ጉዞ በጀግኖች ልጆቿ እውን ይሆናል። ሀገራችን 95 በመቶ የወጪ እና ገቢ ንግዷን በምታካሂድበት ቀጣና፣ የንግድ መስመሯን ከባሕር ላይ ውንብድና እና ከጸጥታ መደፍረስ መጠበቅ አንገብጋቢ ብሔራዊ ጉዳይ ነው።
በአሁኑ ሰዓት ባሕር ኃይሉ የሀገር ውስጥ ስትራቴጂያዊ የውኃ አካላትን፣ በተለይም የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን እና የጣና ሐይቅን ደኅንነት በልዩ የማሪን ኮማንዶዎች በንቃት እየጠበቀ ይገኛል።
በታሪክ አጋጣሚ ፈርሶ የነበረው ባሕር ኃይላችን ዛሬ ከውርደት ወጥቶ የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ዳግም በክብር ተመልሷል፤ ይህም ለወደፊት ትውልድ የውኃ ላይ ሉዓላዊነት የማይነቃነቅ አስተማማኝ መሠረት ነው።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: