በኢትዮጵያ ባህላዊ የሕንፃ ጥበብ ውስጥ "ካስማ" መላው መዋቅር እንዳይደርመስ አጽንቶ የሚይዝ የማዕከል ዋና ደጋፊ አምድ እንደሆነ ይታወቃል። ይህንን ባህላዊ ብያኔ ወደ ሀገር መንግሥት ግንባታ እና ብሔራዊ ደኅንነት ስናመጣው፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሀገራችንን ደግፎ የያዘ የማይበገር የብረት ካስማ መሆኑን በተግባር አስመስክሯል።
ሀገራችን በታሪኳ አያሌ የውስጥ እና የውጭ የህልውና ፈተናዎች፣ የጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረቶች እና ወረራዎች በተደቀኑባት ዘመናት ሁሉ፣ ነፃነቷን እና ግርማ ሞገሷን ጠብቃ እንድትቆም ያስቻላት ዋነኛ መዋቅራዊ ምሰሶ ወታደራዊ ኃይሏ ነው።
ሠራዊቱ በ1900 ዓ.ም በዘመናዊ መዋቅር ከመደራጀቱ በፊት፣ የሀገር ሉዓላዊነት ዘብ የነበረው ራሱ ጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነበር። በዚያ ዘመን መደበኛ እና ዘመናዊ ወታደራዊ አደረጃጀት ባይኖርም፣ ኢትዮጵያውያን በሰላም ጊዜ ማረሻቸውን ይዘው ሀገር የሚገነቡ የልማት ዐርበኞች፣ በጦርነት ጊዜ ደግሞ ሀገራቸውን ከጠላት የሚከላከሉ ቆራጥ ተዋጊዎች ነበሩ።
እ.ኤ.አ በ1579 የኦቶማን ኢምፓየር በምፅዋ በኩል ያደረገውን የማስፋፋት ሙከራ ከመመከት ጀምሮ፣ እ.ኤ.አ በ1876 በጉራዕ ጦርነት የተካሄደውን የግብጽ ወረራ ያከሸፈው የሀገር ካስማ የሆነው ይኸው ሕዝባዊ ሠራዊት ነው።
ይህ አኩሪ የዜጎች ተጋድሎ እስከ ታላቁ የዓድዋ ጦርነት የዘለቀ ሲሆን፣ በ1888 ዓ.ም የመላው ኢትዮጵያውያን የተቀናጀ የክተት ሠራዊት የወራሪውን የጣሊያን ኃይል በመደምሰስ ኢትዮጵያን የማትበገር የነፃነት ቀንዲል አድርጓታል።
ከ1900 ዓ.ም በኋላ ደግሞ ይህ ታሪካዊ የሀገር አለኝታነት በዘመናዊ መልክ ተደራጅቶ ጉዞውን ቀጥሏል።
ሠራዊቱ በየዘመኑ ዝግጁነቱን እያሻሻለ ሀገር በፈለገችው ጊዜ ሁሉ "አለሁልሽ" ብሎ በመድረስ የታሪካዊ ጠላቶቻችንን እና የባዕድ ተላላኪ ባንዳዎችን ምኞት እያጨናገፈ ጠላትን ሲያሳፍር ኖሯል።
ይህ የሀገር ካስማነት ሚና በጦር ሜዳ ውጊያ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ በተለያዩ ጊዜያት የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሲከሰቱ ቀድሞ በመድረስ የዜጎችን ሕይወት እና ንብረት በመታደግ የሕዝብ ደኅንነት ዋስትና መሆኑን በተግባር አሳይቷል።
የሠራዊታችን አለኝታነት በሀገር ውስጥ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ለሰው ልጆች ሁሉ የሚተርፍ ነው።
ሠራዊታችን በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በሩዋንዳ፣ በቡሩንዲ፣ በላይቤሪያ፣ በዳርፉር እና በአብዬ ባከናወናቸው አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የኢትዮጵያን ስም ከፍ አድርጓል።
በአሁኑ ወቅት ሠራዊቱ የደረሰበት ተቋማዊ ቁመና እና በሪፎርም ያመጣቸው ስኬቶች ደግሞ አስተማማኝ ካስማነቱን ከምንጊዜውም በላይ አስረግጠዋል።
በተካሄደው ጥልቅ ተቋማዊ ሪፎርም ሠራዊቱ ራሱን ከፖለቲካዊ ወገናዊነት በማላቀቅ፣ ለሕገ-መንግሥቱ እና ለሕዝቦች ደኅንነት ብቻ የሚቆም እውነተኛ የሀገር መከታ መሆን ችሏል።
ዘመኑ የሚጠይቀውን ወታደራዊ ዝግጅት በማድረግ በቴክኖሎጂ፣ በሳይንስ እና በሰው ኃይል ሥልጠና የላቀ ልዕልናን ተላብሷል።
የምድር፣ የአየር እና የባሕር ኃይሉ እንዲሁም የመከላከያ ኢንደስትሪው የገነቡት አስፈሪ ግርማ ሞገስ፣ ሠራዊቱን የኢትዮጵያ ነበልባል ክንድ አድርገውታል።
በዚህም የተነሳ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ተዋግታ ሳይሆን በዝግጅቷ ብቻ የምታሸብር እና በዘመናዊ ወታደራዊ ሠራዊቷ ግርማ የምትከበር ሀገር ሆናለች። ለዚህ ደግሞ የፈሪ ዛቻ ከሚዝቱት በላይ ምስክር የለም።
ጠንካራ መከላከያ የጠንካራ ሀገር ዋስትና እንደመሆኑ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የጠላትን የጥፋት ሐሳብ ገና በጽንሱ የሚያኮላሽ፣ የሀገራችን የሉዓላዊነት ማኅተም እና የሕዝባችን የሰላም ዋስትና ሆኖ ለዘላለም ይኖራል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: