Search

የሕገ ወጡ እና የከሰረው ቡድን የጦርነት ጉሰማ እና የኢትዮጵያ ጽኑ አቋም

ዓርብ ሐምሌ 24, 2018 178

ሕገ ወጡ እና የከሰረው የህወሓት ቡድን የኢትዮጵያን የልማት እና የብልጽግና ጉዞ ለማደናቀፍ በማለም፣ ዛሬም እንደ ትናንቱ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ይገኛል።

ይህ ፀረ ሕዝብ ስብስብ ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ ሕልውናው የተገነባው በግጭት፣ በደም መፋሰስ እና በትርምስ ውስጥ በመሆኑ፣ ያለ ጦርነት መኖር አይችልም።

ሰላም ሲሰፍን እና ሀገር ስትረጋጋ የፖለቲካ ንግዱ ስለሚከስር፣ በማያባራ የጦርነት ጥሪ ሀገርን ለማተራመስ የማይፈነቅለው ድንጋይ፣ የማይሸርበው ሴራ፣ አንግቦ የማይመጣው የባዕድ አጀንዳ የለም። የዚህ ቡድን ብቸኛ የሕልውና ማረጋገጫ ቀመር ግጭት መፍጠር ብቻ ነው።

ነገር ግን፣ የቡድኑ የጦርነት ጩኸት ዛሬ ላይ አድማጭ ያጣ ባዶ የገደል ማሚቱ ሆኖ ቀርቷል። በአሁኑ ሰዓት ይህ እኩይ ስብስብ ለኢትዮጵያ ስጋት ለመሆን የሚያስችል አቅምም፣ የሕዝብ ድጋፍም ሆነ ችሎታ የለውም።

የትግራይ ሕዝብ የቡድኑን እውነተኛ የጥፋት ገጽታ እና የፖለቲካ ቁማር በሚገባ ተረድቷል። ማኅበረሰቡ ነቅቷል፤ ከእንግዲህ ለዚህ የጥፋት ኃይል የቡድን ጥቅም ሲል የሚገብረው አንዳችም ነገር እንደሌለ በተግባር እያሳየ ነው። የቡድኑ የጥፋት ዜማ ጊዜ ያለፈበት መሆኑን ሕዝቡ አረጋግጧል።

በተለይም የማያባራው ጦርነት እናቶችን ክፉኛ አስመርሯል። የትግራይ እናቶች "ጦርነት በቃን፤ ሞት በቃን!" በማለት በዕንባ እና በዋይታ ምሬታቸውን በግልጽ እያሰሙ ነው። ዳግም ልጆቻቸውን ለትርጉም አልባ እልቂት እና ለቡድኑ የሥልጣን ማቆያነት አሳልፈው እንደማይሰጡ በቆራጥነት እያሳዩ ነው። "ልጄን አልገብርም" የሚለው የእናቶች ጩኸት የቡድኑን የጦርነት ጉሰማ ገደል እያስገባው ነው።

በሌላ በኩል፣ የትግራይ ወጣት የቡድኑን የጦርነት ጥሪ በማውገዝ እና የሞት አዋጁን በመጣስ በነቂስ እየሸሸ ይገኛል። ይህ የወጣቱ የሽሽት እና የማምለጥ እርምጃ፣ ጦርነት እንደማይፈልግ እና የቡድኑ የጥፋት ተላላኪ እንደማይሆን የሚያረጋግጥ የተግባር ምላሽ ነው። ወጣቱ የጥፋት መሣሪያ መሆንን ትቶ፣ የሰላም እና የሕይወትን መንገድ መርጧል።

በአንጻሩ፣ የኢትዮጵያ የሰላም አቋም እጅግ የጸና እና የማይናወጥ ነው። መንግሥት የጀመረውን የሰላም፣ የልማት እና የብልጽግና ጉዞ አጠናክሮ ቀጥሏል።

ኢትዮጵያ የዜጎቿን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕረፍት ለማረጋገጥ ሌት ተቀን እየሠራች ባለችበት በዚህ ጊዜ፣ የሕገ ወጡ ቡድን የጦርነት ጩኸት ከተያያዘችው የዕድገት ጎዳና ሊያስተጓጉላት ከቶ አይችልም።

ሕዝቡም ሆነ ወጣቱ የሰላምን ዋጋ ተገንዝበው ፊታቸውን ወደ ልማት ባዞሩበት በዚህ ብሩህ ዘመን፣ የሕገ ወጡ ቡድን የጦርነት ጥሪ የመቃብር አፋፍ ላይ የሚደረግ የባዶነት ጩኸት እና የተስፋ መቁረጥ ምልክት ሆኖ ይቀራል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: