የኢትዮጵያ ህዝቦች በዘመናት መካከል አብረው ሲኖሩ በብዙ መልኩ የተጋመዱ፣ የተሳሰሩ፣ የተጋቡ፣ የተዋለዱ እና በጋራ የኖሩ ናቸው። በተለይም ደግሞ አማራን እና ኦሮሞን ስንወስድ፣ በአቀማመጣቸው እና በቁጥራቸው ከፍ ስለሚሉ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ መለስ ብለን እያንዳንዱን አንጓ ብንመዝን፣ በሦስት ዋና ዋና መንገዶች በስፋት የተጋመዱ መሆናቸውን እናያለን። እነዚህም ማህበራዊ ጋብቻ፣ የፖለቲካ ጋብቻ እና ባህላዊው ጉዲፈቻ ናቸው። ግለሰቦች ለንግድ እና ለውትድርና ሲንቀሳቀሱ አንዱ ከአንደኛው እያገባ የመዛመድ ልምዳቸው ሰፊ ሲሆን፣ በፖለቲካውም ወንበር ለማጽናት ሰፋፊ የፖለቲካ ጋብቻዎች ተፈጽመዋል። ብዙዎች በነገሥታት ደረጃ የምናያቸውን ጨምሮ በጉዲፈቻ ምክንያት አብረው ያደጉና ባህል የተጋሩበት የቆየ ልምድ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ጸንቶ ይገኛል።
የዘመናት የመስተጋብር እና የውህደት አሻራዎች
ጥቂት መቶ አመታት ወደኋላ መለስ ብለን የኢትዮጵያን ታሪክ ብንመለከት የዚህን ጥልቅ ትስስር እውነት እናገኛለን። 350 አመት ገደማ የቆየው የሸዋ ሱልጣኔት በመንግስትነት በፈጠረበት አካባቢ ላይ በስፋት ኦሮሞዎች፣ አማራዎች፣ አርጎባዎች፣ ጉራጌዎች እና ሐዲያዎች አብረው የኖሩበት ነበር። ኋላም ከ130 አመታት በላይ የቆየው እና ከሸዋ እስከ ዘይላ የሚዘረጋው የኢፋት ሱልጣኔት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የህዝቦች መስተጋብር እንደነበረ ታሪክ ይናገራል። ከጎንደር ዘመነ መንግስት በፊትም በአጼ ሰርጸ ድንግል ዘመን እስከ ምጽዋ በነበረው ዘመቻ ሰፊ ጦር ተንቀሳቅሶ ስለነበር፣ በዚያ ሂደት ውስጥ ከማዕከል ወደ ሰሜን ብዙ መዋለዶች እና መዋሀዶች ተፈጥረዋል።
የጎንደር ዘመነ መንግስትን ብቻውን ወስደን ብናይ፣ የነዚህ ህዝቦች በዘመናት መካከል በፖለቲካ ጋብቻ፣ በጉዲፈቻ እና በነበራቸው ውህደት በደንብ ማየት እንችላለን። አጼ ሱስንዮስ በኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ ያደገ እና ከዚያ ዘምቶ ወደ ዙፋን የመጣ መሪ ነበር። በኋላም እነ አፄ ፋሲልን እና እያሱን ብንወስድ ውህደት፣ ጉዲፈቻ እና ጋብቻ የሚታይባቸው ነገሥታት ናቸው። ከጎንደር ዘመን በኋላ ከመቶ አመት በላይ የቆየው የየጁ ስርወ መንግስት (ዳይናስቲ) ውስጥም ከየጁ እየተነሱ ወደ ጎንደር እና ጎጃም ሰፊ ውህደቶች ነበሩ። በወሎ፣ ጎንደር፣ ጎጃም እና ሸዋ መካከል ሰፊ እንቅስቃሴ እንደነበረ የሚያሳዩት እነ ራስ አሊ ቀዳማዊ፣ ራስ አሊ ኃይሉ እና ራስ ጉግሳ የነበሩባቸው ዘመኖች የዚህ ማሳያ ናቸው።
ከዚያም በኋላ ከ200 አመት በላይ የቆየው የዋረሂመኖ ስርወ መንግስት በተለይ በደቡብ ወሎ አካባቢ በነበረው ቆይታ ወደ ሸዋ፣ ጎንደር እና ጎጃም ከፍተኛ ውህደት እንደነበረ ያሳያል። በዚያ ዘመን ውስጥ ስማቸው ገኖ ከሚነሱ ሰዎች አንዷ ወርቂቱ ስሟ ጎልቶ ሲነሳ፣ እነ ራስ ሚካኤልም ይጠቀሳሉ። ታሪክ የሚያሳየው እነዚህ ህዝቦች በስፋት አብረው ሲዘምቱ፣ አብረው ሲዋጉ፣ አብረው ሲያለሙ እና አብረው ሲያጠፉ ተዋህደው የነበሩ ህዝቦች መሆናቸውን ነው።
ዘመናዊት ኢትዮጵያን የማጽናት የጋራ የደም ዋጋ
ወደ ቅርብ ዘመን መጥተን ለማየት ብንሞክር፣ ዘመናዊት ኢትዮጵያን ታሪክ ያየ ሰው ከነዚህ ህዝቦች ውህደት ውጤት ውጪ ሊያየው አይችልም። ምኒልክ ካለ ጎበና፣ ጎበና ካለ ምኒልክ፣ ዘመናዊት ኢትዮጵያን መፍጠር የሚችሉበት ምንም አይነት እድል አልነበረም። እነዚህ ሰዎች ተዋህደው ነው ሀገር የፈጠሩት። ብዙ ጊዜ ወደ ደቡብ ያለው ግጭት ይነሳል እንጂ የሸዋው ሀይል ጎጃም ውስጥ ከራስ አዳል በኋላም ከንጉስ ተክለሃይማኖት ጋር፣ ወሎ ውስጥ ከራስ ሚካኤል ጋር፣ እንዲሁም አርሲ እና ወላይታ ላይ ተጋጭቷል። ከሸዋ እየተነሳ ወደ ሁሉም አቅጣጫ ነበር ዘመቻ የሚካሄደው። ይሄንን ዘመቻ የመሩት ንጉሱ ምኒልክ ቢሆኑም፣ ጦር አዝማቹ ደግሞ ጎበና ነበሩ፤ ይህም ሀገሪቱ በውህደት የተሰራች መሆኗን በግልጽ ያሳያል።
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ መለስ ብሎ የሚኮራበትን የአድዋን ታሪክ ብናነሳ ምኒልክ ከገበየሁ ውጪ፣ ምኒልክ ከባልቻ ውጪ አልሰሩትም። በውህደት የተሰራ የጋራ ድል ነው። በጋራ የተፋለምንበት፣ ለአንዲት ውድ እና የከበረች ሀገር ዋጋ ከፍለን ለማኖር ሀገራችንን እና የጋራ ህልውናችንን አስቀድመን በጋራ ዘምተን፣ በጋራ ሞተን ያጸናናት ሀገር መሆኗን ያሳያል። በህዝቦች ደረጃም ቢሆን አርሶ አደሮች በፊውዳሉ ስርዓት ላይ ያደረጉትን ማመፅ ብንመለከት የጎጃም ገበሬዎች አመፅ እና የባሌ ገበሬዎች አመፅ የሚሉ ታሪካዊ ተጋድሎዎችን እናገኛለን።
እስከ በኋላም ድረስ ባለው ታሪክ ውስጥ እነዚህ ሁለት ህዝቦች ለዘመናት አብረው ሲዘምቱ፣ ሲጋቡ፣ ሲነግዱ እና በብዙ ሲዋሀዱ የኖሩ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ታሪክ በግልጽ ያስቀምጣል። ይህ ባህሪ በሁለቱ ብሔሮች ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ ብዙዎቹ ላይ እንደዚህ አይነት የመዋሀድ እና አብሮ የመኖር ልምዶች በስፋት ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ። ከዚህኛው ለውጥ ቀደም ብሎ ኢትዮጵያ ውስጥ በተደረጉ ለውጦች የአማራ ህዝብ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ ለውጥ እንዲመጣ፣ የፖለቲካ ስርዓታችን እንዲሻሻል፣ የኢኮኖሚ ጉዟችን እንዲፋጠን እና ህዝቦችን ያቀፈ እንዲሆን ትግል ሲያደርግ ነበር። በ66ቱ፣ በ83ቱ እና በ2010ሩ ለውጦች ውስጥ የአማራ ህዝብ ለውጥ መጥቶ ለመሻሻል እና ለማደግ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጉን ታሪክ ይናገራል።
የተዘጋውን የፖለቲካ ቤት ማናፈስ እና የገጠሙ ፈተናዎች
ከለውጥ ማግስት የነበረው ጉዞ የአማራ ህዝብ እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በከፍተኛ ተስፋ የተሞላበት፣ ሁለት እጁን ዘርግቶ ለውጡን የተቀበለበት እና ሀገር አፀናለሁ የሚል ህልም የታየበት ሁኔታ ነበረ። ከ2010ሩ ለውጥ ቀደም ብሎ በነበረው የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ የመዘጋት፣ የመታፈን እና የመታሸግ ምልክቶች ነበሩ። አንድ ሰው ዝም ባለ ጊዜ ከቤቱ ወጥቶ ወደ ራሱ ቤት ቢመለስ ያ ቤት ተዘግቶ የቆየ እንደሆነ፣ ልክ በሩን ከፍቶ ሲገባ ቤቱ ያፍናል፣ ይሸታል። የመጀመሪያው ስራው መስኮት ከፋፍቶ ንፁህ አየር እንዲገባ፣ ቤቱን እንዲናፈስ ማድረግ ነው። ያንን መናፈስ ሳታደርግ እንደ ከዚህ ቀደሙ የለመድከውን የኖሮ ዘይቤ ማስቀጠል አትችልም። ፖለቲካችንም ኢኮኖሚውን ጭምር ታፍኖና ተዘግቶ ስለቆየ ከፈትፈት አድርጎ ማናፈስ ይፈልግ ነበር።
በዚያ በነበረ ሁኔታ መቀጠል ስለማይቻል፣ እንደ ለውጡ እንደመጣ መስኮቶቻችንን ከፋፈትን። እነዚያ መስኮቶች ከእስር ቤት፣ ከውጭ ሀገር፣ እንዲሁም የፖለቲካ ዝንባሌ የማይታይባቸው ሰዎች የፖለቲካ ስሜት እንዲላበሱ በማድረግ ብዙ አይነት ሰዎች በፖለቲካ አውድ ውስጥ ለመሳተፍ ሙከራ አድርገዋል። ነገር ግን አንድ ሰው የተዘጋ ቤቱን ንፁህ አየር ለማስገባት መስኮት ሲከፍት ንፁህ አየር ብቻ አይደለም ወደ ቤቱ የሚገባው። አብረው ትንኞች እና ቢንቢዎች ይገባሉ። ቢንቢ በሳይዟ በጣም ትንሽ ብትሆንም ድምጿ እንዳትተኛ ታውካሃለች፣ ትቀሰቅስሃለች፤ ከዛም አልፎ በመንደፍ ደምህን ትጠጣለች፣ በሽታም ታመጣብሃለች።
እንደዚህ ያለው ሁኔታ በኢትዮጵያ የፖለቲካ አውድ ውስጥ ተፈጥሯል። በማናፈሱ ውስጥ ተቀላቅለው የገቡ፣ ከፍተኛ ድምፅ በማሰማት ለማወክ የሞከሩ፣ ከዛም ሲያልፍ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለመናደፍ እና የኢትዮጵያን ህልውና ለመገዳደር ከሚፈልጉ ሀይሎች ጋር እስከ መሰለፍ የሄዱ ዝንባሌዎች ታይተዋል። በዚያ መከፈት ምክንያት መድረክ አግኝተው ሁኔታው ከተስፋ ወደ ስጋት እንዲገባ ለማድረግ የሞከሩ ሀይሎች በሁሉም ክልሎች፣ በአማራም ክልል ተስተውለዋል። ህዝቡ በከፍተኛ ደስታ የተቀበለውን ለውጥ በኋላ "ምንድን ነው የመጣብን?" የሚል ድንጋጤ እና ስጋት ያደረበት ቢሆንም፣ ነገር እየተገለጠ ሲሄድ የመደመር መንገድ ብቸኛው አማራጭ መሆኑን፣ ለመበልጸግ የሚደረገው ጥረት ተገቢ መሆኑን ያመነ ሀይል ሆኗል። ይህንን በሚያረቅ፣ በሚያድስ፣ በሚያሻሽል እና በሚያሰፋ መንገድ መሄድ ብቻ ነው እንደ ሀገር ተከባብረን እና ተዋደን አንዲት ታሪካዊት ሀገር ማጽናት የምንችለው።
የኦሮማራ ንግግር መነሻ እና የህዝብን የልብ ትርታ ማድመጥ
ይህ እሳቤ ከለውጡ ማግስት ሳይሆን ትንሽ ወደ ኋላ ይሄዳል። በ2003 ክረምት የከፍተኛ አመራሮች ስልጠና ወቅት ከአንዳንድ የአማራ ጓዶችና አመራሮች ጋር ንግግር የጀመርንበት ጊዜ ነበር። ያ ንግግር ትርክትን ማደስ ያስፈልጋል፣ መካከላችን ያለውን ግድግዳ ማፍረስ ይኖርብናል፣ የነበረውን ታሪካችንን ፈትሸን እና መርምረን ወደ ምንተባበርበት፣ ወደ ምንተጋገዝበትና በጋራ ወደ ምንቆምበት ቆመና ካልተቀየርን የኢትዮጵያ ነገዋ አስጊ ነው የሚል ነበር። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩ የተለዩ ሀይሎች መፈጠር፣ መጣመርና ያልተቀደሰ ጋብቻ ሲታይ ያንን ሁኔታ ያስታውሳል።
እኛ የነበረን ውይይት በሦስት አንጓ የተከፈለ ነበር። መገንባት የምንፈልገው ሀገር አለ፣ እዚያ ጋር ለመድረስ ግን ምን እንዳለን ማወቅ አለብን፣ ምን እንዳለን ከማወቃችን በፊት በሁኔታዎች ላይ ያሉን እምነቶች ምን እንደሆኑ እንወያይ ነበር። በታሪክ ምልከታችን፣ በኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ እና በኢትዮጵያ ህዝቦች በእኩል የመጠቀምና የማደግ ሁኔታዎች ላይ ያለንን እምነት ማወቅ ጠቃሚ ነበር። በመጀመሪያ እምነቶቻችንን በሚመለከት ረዘም ላለ ጊዜ ተወያይተን መግባባት ሲታይ፣ ያላት ኢትዮጵያ ምን እንደሆነች፣ እኛ ምን እንደጣለን እና ምን እንደምናመጣ ከለየን በኋላ ኢትዮጵያን በምን መልክ እንገንባት በሚለው ላይ እንወያይ ነበር። አሁን ብዙዎቹ እምነቶቻቸውን ከደል በኋላ ስለሚያደርጉ፣ ትንሽዬ ነገር ሲመጣ መሰረቱ የተስተካከለ ስላልነበረ ቶሎ ይፈርሳል። ሁልጊዜም ውህደት ሲፈጠር ግለሰቦች፣ ፓርቲዎች እና ቡድኖች መነጋገር ያለባቸው እምነትን ነው። በምን መነጽር ትናንትን፣ ዛሬንና ነገን እንደምናይ ካልተግባባን በጋራ መቆም ጥላትን ያሰነብት ይሆናል እንጂ ብዙም ፋይዳ አይኖረውም።
ከለውጡ ጥቂት ወራት በፊት በኦሮማራ እንቅስቃሴ ባህርዳር መጥቼ ከሚዲያ ጋር ቆይታ አድርጌ ነበር። የሁለቱን ህዝቦች በጋራ ለዘመናት መኖርና በተግባር መንፈስ መስራት ኢትዮጵያን ለመታደግ ያለውን ፋይዳ በጉልህ የሚያሳይ ነበር። የኦሮማራ እንቅስቃሴ ብዙ የሚጠላና ጥቃት የነበረበት እንቅስቃሴ ቢሆንም፣ ከዛ እንቅስቃሴ በኋላ የለውጥ ፍላጎት ልክ እንደ በልግ ዝናብ ምንም ድምፅ ሳያሰማ በሚመጣበት ሰዓት ነገሮች ሁሉ ፈጣን ነበሩ።
የእንቅስቃሴው ዋነኛ ምክንያት ለውጥ ሲደረግ የህዝብን የልብ ትርታ በበቂ ደረጃ መገንዘብ ካልተቻለ ረዘም ላለ ጊዜ ለውጥን መምራት ስለማይቻል ነው። የመጀመሪያው ጉዞ ወደ ጎንደር ነበር። ጎንደር ከለውጥ ቀነዲሎች አንዷ ናት። "የኦሮሞ ደም የኔም ደም ነው" ብለው የተነሱ ወጣቶች የታዩበት፣ ታሪኳን መለስ ብላ ለማየት የቻለችና በህዝቦች መካከል ያለውን ውህደት ያየች ከተማ ነበረች። ይህ አባባል መፈክር ብቻ ሳይሆን ጎንደር ውስጥ በስፋት የኦሮሞ ደም እና ጋብቻዎች አሉ። አቀባበሉ ያማረ፣ ተስፋ የሞላበት እና ኢትዮጵያዊነትን በሚገባ ያሳየችበት ከተማ ነበረች። በዚያም ብዙ ጥያቄዎች ስለነበሩ እነዚያን ከሞላ ጎደል ለመመለስ፣ ለማብራራት እና ለመቀበል ጥረት ተደርጓል። ከዚያ በኋላ በባህርዳር፣ በደሴ፣ በኮምቦልቻ፣ በደብረ ብርሃን፣ በወልዲያ፣ በደብረ ማርቆስ እና አዲስ አበባ ላይ በተደጋጋሚ በመወያየት ህዝቡ ምን ይፈልጋል የሚለውን ለማየት ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል።
የቻይናው ሪፎርም ትምህርት እና የኢትዮጵያ የመደመር መንገድ
ታፍኖ በቆየ ፖለቲካ ውስጥ የሚደረግ ለውጥ ከህዝብ ጋር መወያየትና የህዝብን የልብ ትርታ ማድመጥ የሚያስፈልግበት ምክንያት፣ የቻይናን ለውጥ ከማኦ በኋላ ዴንግ ሲያኦፒንግ ሲመጣ ከነበረውን ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል። ፖለቲካውና ኢኮኖሚው የታፈነ፣ ረሀብና ችግር የነበረበት፣ ከ600 ሚሊዮን ያላነሰ ህዝብ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ የሚኖርበት ሁኔታ ነበር። ዴንግ ያንን ለመፍታት በሶሻሊዝም ያለውን እሳቤ ጥሶ ከሌሎች ኢምፔሪያሊስቶች ብሎ ከሚጠላቸው ሀይሎች ጋር በትብብር ለመስራት ወሰነ። ነገር ሲከፋፈት ሙስና እና የዋጋ ግሽበት በጣም አደገ። ያን ለመቆጣጠር ጥረት በሚያደርጉበት ሰዓት ወጣቶቹ ኢኮኖሚያችን የሚከፈት ከሆነ ፖለቲካችንም ልክ እንደነሱ ዴሞክራሲ ይሁን፣ ምርጫ ይኑረን የሚል ጥያቄ አነሱ።
በነዴንግ እምነት ጠንካራ መንግስት እና የታነጸ ፓርቲ ረዘም ላለ ጊዜ የሚጸና መንግስት ካልፈጠርን ችግሩን አንፈታም የሚል እምነት ስለነበራቸው፣ ጥያቄው በቀላሉ ምላሽ የሚያገኝ አልነበረም፤ ወደ ደም መፋሰስም አምርቶ ነበር። በእኛ ሁኔታ አስቸጋሪ የሆነው ነገር ኢኮኖሚውን ከፍተን ፖለቲካውን ብንተው፣ ወይም ፖለቲካውን ከፍተን ኢኮኖሚውን ብንተው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ መቀየር አንችልም። ስለዚህ ህዝብ አወያይተን የልብ ትርታን ካደመጥን በኋላ፣ እንዴት አድርገን ነው ሁለት ዋና ዋና የስብራት መንስኤዎቻችንን በመክፈት የምናስባትን ሀገር ልንሰራ የምንችለው የሚለውን ዲዛይን ለማድረግ ያ ውይይት በእጅጉ አስፈላጊ ነበር። በሁሉም የሀገሪቱ ጫፎች የኢትዮጵያ ፍላጎት ከሞላ ጎደል የሚቀራረብ መሆኑን አይተን፣ መደመር በተሟላ ቅርጽ ወጥቶ ብቸኛው መንገድ በተደመረ መንገድ ወደ ብልጽግና መጓዝ ነው ወደሚል መንግስታዊ ነድፍ ገባን።
የሰኔ 15ቱ ክስተት መንስኤዎች እና የተዉት ጠባሳዎች
የሰኔ 15ቱ ክስተት በመሰረቱ ከሁለት ጉዳዮች የመነጨ ነው። አንደኛው ስሁት ግምገማ ነው። አንድ ነገር ለማሳካት የምትሰራው ግምገማ በበቂ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ ከሆነ፣ ጉጉት ይቀድምና መሻት ይፈጥንና ወደዚያ ለማድረስ የሚገባህን መንገድ በትክክል ዲዛይን ሳታደርግ ጥፋት ታመጣለህ። ሁለተኛው ችግር በሁለት እግር ማነከስ ነው። ለውጥና የህዝብ አደራ ተቀብሎ በሌላ መንገድ ደግሞ ያልተቀደሰ ጋብቻ ከመደዳኛ ሀይሎች ጋር አድርጎ እዚሁም እዚያም ለመሆን የሚፈለግ ሁኔታ በአንዳንድ ሰዎች ይታይ ነበር። በአንድ መንግስት ወይም ፓርቲ እቅድ የሚመራ ስብስብ ሳይሆን፣ እቅዱን ከተለያየ ምንጭ የሚወስድ ሀይል ያለበት፣ በጋራ የሚነጋገርና በዛ ሂደት ውስጥ ጥፋት ሊያመጣ የሚችል ክስተት ሆኗል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ስልጣን ሲመጣ በሀይል፣ አልጋ ሳይጸና የመገዳደር ፍላጎት የባህላችን አንዱ አካል ነው። በልጅ እያሱ ዘመን፣ በጃንሆይ ጊዜ የታሳስ ግርግር፣ 66 ላይ ያጋጠመው፣ በደርግ ዘመን በ1981 ያየነው፣ በኢህአዴግ ዘመን በ2001 አካባቢ የተንጸባረቀው፣ እንዲሁም በእኛም ጊዜ ከለውጡ ሁለት ሦስት ወር በኋላ በመስቀል አደባባይ የተካሄደው መሰል ሙከራ የዚህ ማሳያ ናቸው። ሁልጊዜም በሀይል ፍላጎትን ማሳካትና ሰው በመግደል ስልጣን ለመውረስ መሞከር ነበረ። የሰኔ 15ቱን ለየት የሚያደርገው በክልልና በከተማ ደረጃ ዝቅ ብሎ ለመፈጸም የተሞከረ ሙከራ መሆኑ ነው።
ይህ ክስተት በሦስት መንገድ ጠባሳ ጥሎብን አልፏል፡-
አንደኛው ባጣናቸው ግለሰቦች ነው። የለውጥ ሀይል የሆኑ ከፍተኛ ሚና ያላቸውን ሰዎች ያሳጣ ክስተት ነው። ለምሳሌ ዶክተር አምባቸው ከ2003 ጀምሮ ንግግር እናደርግ ነበር ካልኳቸው ሰዎች አንዱ ሲሆን፣ ለለውጥ ከፍተኛ ጉጉት የነበረውና ሁለታችንም የካቢኔ አባላት ሆነን በደንብ እንወያይ ነበር። ጄነራል ሰዓረም ቀደም ብሎ በአንድ ክፍል ውስጥ አብረን የተማርነው፣ ረዘም ያለ ጊዜ ትውውቅ ያለንና ቅርብ የነበርን ሰው ነው። የጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙንና የደህንነት ሀላፊውን በአንድ ጀምበር ለማንሳት የነበረው ውሳኔ ከመጀመሪያው ከእቅዱ ጀምሮ የተሳተፈበት ብቸኛው ሰው ሰዓረ ነበር። በዚያ ደረጃ ለለውጥ የሚታመኑና ቢቆዩ ብዙ የሚያበረክቱ ሰዎችን አጥተናል።
ሁለተኛው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የፈጠረው የመተማመን ስብራት (Political trust) ነው። በሰዎችና በቡድኖች መካከል አብሮ የመተማመን ዝንባሌው በእጅጉ እንዲቀንስ አድርጓል። አብረህ ስለ ሀገር ከምትመክረው ሰው አደጋ ያጋጥመኛል እያሰብክ መምከር በእጅጉ መተማመንን የሚቀንስ መጥፎ ጠባሳ ነው።
ሦስተኛው የፖለቲካ ባህላችንን አበላሽቶታል። ከንግግርና ከውይይት ይልቅ በመሳሪያና በጉልበት ግለሰቦችን በማፈንና በመግደል ስልጣን ማረጋገጥን የሚያስቀጥል መሆኑ በጠባሳነት ይታያል። ክስተቱ ይበልጥ የሚያሳዝነው፣ ገዳይም ሟችም ሁለቱንም ሀይሎች በጀግንነት ያወሳ የፖለቲካ ትወና የታየበት መሆኑ ነው። ታሪክን እንዳለ አስቀምጦ ከመልካሙም ከስህተቱም መማር ሲገባ ታሪክን እየመረጡና እያንሻፈፉ የማቆየት ጉዳይ አሁን ላለንበት አጠቃላይ ውጥንቅጥ ዋናው መሰረት ነው። በብሔርተኝነትና በአውራጃዊነት ስሜት ታሪኩን ተንሻፎ መጻፍ ነገ ልጆቻችን ዋጋ ሊከፍሉበት የሚችል ጉዳይ ነው።
እለቱ ቅዳሜ ማምሻ ላይ የተፈጠረ በመሆኑ፣ መረጃው እንደሰማሁ ለሚዲያ መናገር አለበት በሚል ፋና፣ ኢቢሲ እና አሚኮ ተጠርተው ነበር። ፋና እና ኢቢሲ በዚያ ፍጥነት ስላልመጡና አሚኮ ቅርብ ስለነበር ወዲያው መጣ። አሚኮ ወስዶ ለሁሉም ሊያከፋፍል ስለሚችል መግለጫው ለአሚኮ ተሰጠ። በኋላ ግን "ባህርዳር ላይ ሆኖ መግለጫ የሰጠው" የሚል የሴራ ትንታኔ ተቀይሯል። እንደዚህ ያለው ከእውነት የተፋታ፣ ለዛሬም ለነገም የማይበጅና ውስጥ እያወቀ የሚዋሽ ነገር ጥፋት ብቻ ነው የሚያመጣው፤ ክስተቱም እንደ ጥቁር ጠባሳ የሚወሰድ መጥፎ ክስተት ነው።
የጎራ መቀያየር ምክንያቶች እና የትዕግስት አስፈላጊነት
ለውጡን በመደገፍ እና ባለመደገፍ ጎራ የመቀያየሩ ጉዳይ በአማራ ዲያስፖራ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በሁሉም ዲያስፖራዎችና በሀገር ውስጥም የሚያጋጥም ነው። ጎራ መቀያየሮች በሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች ያጋጥማሉ፡-
አንደኛው የተሳሳተ ስሌት የነበራቸው ግለሰቦች ናቸው። ለውጡ ሲመጣ በያሉበት ሆነው "ይሄን ለውጥ ያመጣሁትና የዚህ ለውጥ ባለቤት እኔ ነኝ፤ እኔ በማስበው መንገድ መሄድ አለበት" ብለው ያመኑ ግለሰቦች ነበሩ። ለውጡ የብዙ ሰዎች ጥረት፣ ብዙዎች ዋጋ የከፈሉበትና በማስተባበር የሚመራ እንጂ የግለሰቦች ፍላጎት ለማሳካት የሚፈጸም አለመሆኑን ሲረዱ የጎራ ለውጥ አሳይተዋል። አንድን ለውጥ በራስ መመዘኛ ብቻ ማየት ስትጀምርና ሌሎችን ማድመጥ ሲያቅት ይህ ችግር ያጋጥማል።
ሁለተኛው ለርካሽ አላማ የሚቆሙ ሰዎች ናቸው። ከዩቲዩብ ንግድ ጋር የሚያያዝ ወይም በአንዳንድ ሀገራት የጥገኝነት ፈቃድ ለመጠየቅ መቃረንን፣ ማሳደብንና ማብጠልጠልን ብቸኛ መንገድ አድርገው የሚያስቡ ሰዎች አሉ። ኢትዮጵያ ሲመጡ "እኛ እንዲህ አልመሰለንም በጣም ተጸጽተናል" ይሉና፣ ትንሽ ቆይተው የግድ የገንዘብ ተቀማጭ ስለሆነ መልሰው ያ ባህሪ ሲያገረሽባቸው ይታያል።
በሦስተኛ ደረጃ ግን እውነተኛ ጥያቄ ያላቸው ሰዎች አሉ። በአንዳንድ ጉዳይ ላይ እውነተኛ ጥያቄ አንስተው በበቂ ደረጃ ምላሽ ያላገኙ ሲመስላቸው ስሜቱ የሚሰማቸው ሰዎች አሉ፤ ያ የኛም ድክመት ያለበት ሊሆን ይችላል።
እውነተኛ ጥያቄ ያላቸው ሰዎች ቅርብ ብለው ማየት፣ መምጣት፣ መመልከት፣ መጠየቅና አብረው መስራት አለባቸው። ለውጥ ዳር በማቆም ብቻ አይሳካም፤ መሳተፍ ይፈልጋል። ወንዝ ለመሻገር አብሮ መዋኘት እንጂ ውሃውን ዝም ብሎ መውቀስ አይበጅም፣ አይጠቅምም። በዋና ውስጥ በጣም ብዙ ፈተና ይኖራል፤ በዛ ሂደት ውስጥ ነው ትክክለኛውን ነገር የምናገኘው። በተሳሳተ ስሌት ውጤቱን የገመቱ ሰዎች የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ እና ዘመኑን መገንዘብ ያስፈልጋቸዋል። ለውጥ የአንድ ሰሞን ድግስ አይደለም፣ ሂደት ነው። ረጅም መንገድ መሆኑን አምኖ ራስን አጀስት ማድረግ ያስፈልጋል። ጫና መቋቋም የሚሳናቸው፣ ለጊዜያዊ ችግር ሲሉ ሸብረክ የሚሉ ሰዎች ለርካሽ አላማ ሲባል ከቁም ነገር መጉደል የለባቸውም። ታሪክ መስራት የሚያስችል ሁኔታ ካለ ለዚያ መሄድ፣ ያም ካልተቻለ ከታሪክ ቀኝ መቆም እንጂ ለወቅታዊ ችግር ሲባል አቋም በማጣት የሀገርን ጥቅም ማሳጣት አይበጅም፣ ሰላሙና ውጤቱ እስካለ ድረስ እውነታው እየተገለጠ መሄዱ አይቀርም።
ውስብስብ የፖለቲካ ጥያቄዎች እና የዘላቂ መፍትሄ አቅጣጫዎች
ከለውጥ ማግስት ባደረግነው ውይይት በሁሉም የሀገሪቱ ጫፎች የነበሩት ጥያቄዎች በሁለት አንኳር ጉዳዮች ይከፈላሉ፡- የፖለቲካ ጥያቄ እና የመልማት ጥያቄ። የፖለቲካ ጥያቄው በራሱ በሁለት ይከፈላል።
አንደኛው ጊዜ የሚወስድ፣ ዘላቂ መፍትሄ የሚሻ፣ አስተማማኝ ሰላም ማረጋገጥ የሚፈልግና ከአንድ ብሄር፣ ክልል ወይም ፓርቲ በላይ ማሳተፍ የሚፈልጉ ጉዳዮችን የያዘ ነው። ለምሳሌ ህገ መንግስት፣ ሰንደቅ ዓላማ፣ አንቀፅ 39 እና የወሰን ይገባኛል ጥያቄዎች ሙሉ ውይይትንና ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጡ ምላሾችን ይጠይቃሉ። እነዚህ ብዙዎቹ በሀገራዊ ምክክሩ ምላሽ ሊያገኙ እንደሚችሉ ተስፋ እናደርጋለን። በአንድ አካባቢ የተጠየቀውን ጥያቄ እዛው ምላሽ እሰጣለሁ ብትል በሌላ አካባቢ ጥያቄ ሊወልድ ይችላል።
ከዚህ ማሳያ አንዱ የወልቃይት ጥያቄ ነው። ይህንን ጉዳይ ሁለቱም ክልሎች እና የሁለቱም ክልል ህዝቦች ያሳተፈ፣ ያወያየ፣ በህገ መንግስቱ መሰረት በሪፈረንደም የተረጋገጠ ለዘላቂ ሰላም መነሻ የሚሆን ካልሆነ "እድል አግኝቻለሁና አሁን ላድርግ" ብትል ሲቀየር ይበላሻል። በትግራይ በኩል "በጦርነቱ ምክንያት ነው ያንን ቦታ ያጣነው፤ አሁን እየከለከለን ያለው የፌደራል መንግስት ነው" የሚል ጥያቄ ሲኖር፣ ወደ አማራ ክልል ደግሞ ስንመጣ "በህግ አግባብ በተሟላ መንገድ ወደ አማራ ክልል መመለስ ሲገባው የፌደራል መንግስት አልመለሰም" ብለው ያስባሉ።
ይህን ጥያቄ የምንፈታው አንዱን ወገን በማስደሰት ከሆነ ዘላቂ ሰላም አያመጣም፤ የጊዜ ጉዳይ እንጂ መልሶ ግጭት ይፈጥራል። መልሶ ግጭት የሚፈጥርን ነገር ለአጭር ጊዜ እፎይታ መመለስ የመደመር መንግስት መርህ አይደለም። የኛ መርህ ሚዛናዊነት እና ሙሉ ውይይት ነው። ጊዜ ወስደን ተወያይተን፣ ህግንና ስርአትን ተከትለን፣ የህዝቦችን ተሳትፎ አረጋግጠን ብንወስን ለዘላቂው ሰላም ሊያረጋግጥ ይችላል። ሀገራዊ ምክክሩ አራት አመት የፈጀና ብዙ ሺህ ሰዎች የሚሳተፉበት ነው። ኢትዮጵያ የምትሰራው በውይይት፣ በንግግር እና በትግስት ነው። ከአማራ ክልል ጥያቄ አንፃር ከበፊቱ የከፋ ነገር አሁን አለ ብሎ ለመውሰድ ያስቸግራል። በፊት ወደዚያ አካባቢ መጓዝ አይቻልም ነበር፤ ዛሬ ቢያንስ መሄድና መጠየቅ ይቻላል፣ ለመንቀሳቀስ የሚከለክል ነገር የለም። በትግራይም አሳትፈን እነሱም የኛ ወገኖች መሆናቸውን አምኖ፣ ሁለቱንም ህዝብ የሚያሳምን አሸናፊ (Win-Win) አካሄድ ብንከተል ዘላቂ ሰላም ያረጋግጣል።
በሌላ በኩል በአጭሩ ፓርቲውና መንግስት መመለስ የሚገባቸው ብዙ የፖለቲካ ጥያቄዎች ምላሽ አግኝተዋል፡-
- በፓርቲ ውስጥ "ባለቤትና አጋር/ጎረቤት" ተብሎ የነበረውን ክፍፍል በማጥፋት እኩል ተሳትፎ ተረጋግጧል። በፓርላማ በርከት ያለ ወንበር እያለ በፓርቲ ውስጥ ግን እኩል ወንበር ኖሮ የአብላጫ ውሳኔ የማይሰራበት የነበረው የተዛባ አሰራር ተስተካክሏል።
- ክልሎች ከፌደራል መንግስት በህግ የተሰጣቸው ስልጣን ባሻገር ጣልቃ ሳይገባባቸው በነፃነት ልማታቸውን፣ ሰላማቸውንና ፖለቲካቸውን እንዲያራምዱ ተደርጓል።
- በፌደራል መንግስት ቁልፍ ተቋማት (አየር መንገድ፣ ቴሌኮም፣ የባህር ትራንስፖርት ወዘተ) ላይ የነበረው የውክልና እና የአካታችነት ቅሬታ ብዙ ርቀት ተሂዶ ተፈቷል።
- እንደ ገዢ፣ ጨቋኝ እና አጥፊ የሚወስደውን መጥፎ ትርክት ለማረቅና ለማስተካከል ተችሏል።
- በካቢኔ ውስጥ የሚፎካከሩ ፓርቲዎች ገብተው በጋራ ሀገር እንዲመሩ ተደርጓል፤ በፓርላማ ውስጥም ሌሎች ሀይሎች እንዲሳተፉ እድል ተፈጥሯል።
የመደመር መንግስት አራቱ ሀገር-በቀል ምሰሶዎች
አብዮታዊ ዴሞክራሲ ስለ መከላከያ፣ ስለ ህዝቦች እና ስለ መንግስት ያለው እሳቤ እና የመደመር መንግስት ያለው እሳቤ አይገናኙም። የመደመር መንግስት መነሾ ቢያንስ አራት ኢትዮጵያ ውስጥ የምናውቃቸውን መሰረታዊ እምነቶች፣ ልምምዶች እና ባህሎች እንደመነሾ ይወስዳል፡-
- ቅኔ (ለኮሙኒኬሽን)፡- ቅኔ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሰው በሰምና በወርቅ ሚስጢር አዘል በሆነ መንገድ የሚናገርበት ቋንቋ ነው። ያን የማይረዳ መንግስት ከህዝብ ጋር ሊግባባ አይችልም። ህዝብህን ለማድመጥ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚናገርበትን ዜማ እና ልምምድ እንደ አንድ የኮሙኒኬሽን ድልድይ አድርጎ የመደመር መንግስት ይወስደዋል።
- ደቦ (ለትብብርና ልማት)፡- የተበተኑ እውቀቶች፣ የሰው ሀይል እና ካፒታል አሉ። ይህን ሰብስቦና ደምሮ አንድ አዲስ ነገር እንዲከሰት ለመስራት፣ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች "ተባብረን እንረስ" የሚሉበትን የደቦ ልምምድ እንደ አንድ መሰረት እንወስደዋለን።
- ሽምግልና (ለእርቅና ሰላም)፡- በታሪካችን ውስጥ የእምነት፣ የብሄር፣ የመሬትና የስልጣን ግጭቶች ነበሩ። እነዚህን ግጭቶች እየፈታ ያቆየበት መንገድ ሽምግልና፣ ካሳ፣ እርቅ እና ይቅርታ የሚባሉ እሴቶች አሉት። ይህንንም በውስጥ ያሉትን ቅራኔዎች ለመፍታት እንደ መሰረት እንወስዳለን።
- የገዳ ሥርዓት (ለተቋም ግንባታ)፡- በመጀመሪያው ደረጃ ላይ ያለው የሀገር ግንባታ መንገድ ብቻውን በቂ ስላልሆነ የተቋም ግንባታ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ለብዙ መቶ አመታት ከልጅ ልጅ ሲወራረስ የቆየውን የገዳ መንግስታዊ ስርአት እንደ መሰረት እንወስዳለን። ገዳ የስልጣን ገደብንና ግልፅ የስልጣን ክፍፍልን የሚያረጋግጥ፣ የስልጣን አወራረስ ሂደቱ ሰላማዊ የሆነና ሰውን የማዘጋጀት ከፍተኛ ልምድ ያለው ነው።
ለተቋም ገዳን፣ ለኮሙኒኬሽን ቅኔን፣ ለዕርቅ ሽምግልናን፣ አብሮ ተባብሮ ለመስራት ደግሞ ደቦን መሰረት አድርገን ከሀገርኛ እውቀትና ባህል በተመነጨ እሳቤ ላይ ቆመን የመንግስት ስርአቱን ነድፈናል። በእንደዚህ ያለው ጉዳይ በጣም ትላልቅ ምላሾች ተሰጥተዋል፤ ሌላው ደግሞ እኛ ሳንሆን ልጆቻችን የሚመልሱት ጉዳይ ሊኖር ይችላል። ሁሉም ነገር በአንድ ጀምበር ስለማይመለስ አንዳንዱን በትዕግስት ማየት ለአማራም ለሌሎችም ህዝቦች አስፈላጊ ጉዳይ ነው።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: