የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር የዜጎችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በዘላቂነት ለማቃለል የሚያስችለውንና ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል በቀላሉ የሚሳተፍበትን “6400 A” የተሰኘ አዲስ የዲጂታል በጎነት ፕላትፎርም በይፋ አስጀምሯል።
ፕሮጀክቱን በይፋ ያስጀመሩት የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በከተማችን ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለው እና የበርካታ ተጋላጭ ወገኖችን እንባ ያበስንበት ትልቅ የማህበራዊ ልማት ፕሮግራም መሆኑን ገልፀዋል።
ይህ አዲስ የዲጂታል ፕላትፎርም ሀብትን ከብክነት በመታደግና ለታለመለት ዓላማ በማዋል የበርካታ ዜጎችን የኑሮ ጫና ማቃለል የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል።
በድህነት መኖር ተፈጥሯዊ ስሪታችን ባለመሆኑ የጋራ ችግራችንን ተባብረን መፍታት እንዳለብን አፅንዖት የሰጡት ምክትል ከንቲባው፣ መላው የከተማዋ ነዋሪ በዚህ ፕላትፎርም በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ይመር ከበደ በበኩላቸው፣ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በጎነት የከተማዋ ዋና መገለጫና የህብረተሰቡ ጠንካራ እሴት እንዲሆን በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን አስታውሰዋል።
ይፋ የተደረገው የዲጂታል በጎነት ፕሮጀክትም እስካሁን የተገኙ ሰው ተኮር ውጤቶችን ይበልጥ ለማስቀጠል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
በመሆኑም ማንኛውም ዜጋ በቀላሉ ወደ 6400 "A" የሚል አጭር የጽሁፍ መልዕክት በመላክ እና በቀን 1 ብር ብቻ በመለገስ የከተማ አስተዳደሩን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ግብ በጋራ እንድናሳካ በመድረኩ መልእክት ተላልፏል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: