በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ለለውጥ ሂደቱ የሚያሳዩት ድጋፍ መቀያየሩ ከተሳሳተ ስሌት፣ ከግል ጥቅም እና ለጥያቄ ምላሽ ከማጣት የመነጨ ሊሆን እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ይህ የጎራ መደበላለቅ በአማራ ዳያስፖራ ብቻ ሳይሆን በሁሉም አካባቢዎች ተወላጆች ዘንድ በስፋት የሚታይ ዝንባሌ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ ወጥ ያልሆነ ተለዋዋጭ ድጋፍ ሦስት መሠረታዊ መነሻዎች እንዳሉት ጠቅሰው፣የመጀመሪያውና ዋነኛው የተሳሳተ ስሌት የነበራቸው ግለሰቦች የሚያሳዩት ባሕሪ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገራዊ ለውጡን በግላቸው እንዳመጡት በማሰብ የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ ለማሳካት የሞከሩ አካላት፣ ለውጡ የብዙዎች ጥረት እና መስዋዕትነት ውጤት መሆኑን ሲረዱ እና ፍላጎታቸው ሳይሳካ ሲቀር ጎራቸውን እንደሚቀይሩ አብራርተዋል።
ሂደቱን በግል መነጽር ብቻ በመመልከት የሕዝብን ፍላጎት ለማድመጥ ፈቃደኛ ያልሆኑ ኃይሎች መኖራቸውንም አንስተዋል።
በተጨማሪም ዩቲዩብን ጨምሮ ከተለያዩ የዲጂታል ትስስር ገጾች ለሚገኝ የገንዘብ ጥቅም እንዲሁም በተለያዩ ሀገራት የፖለቲካ ጥገኝነት ለማግኘት ሲሉ ብቻ ለውጡን ለማንቋሸሽ የሚሰለፉ አካላት መኖራቸውን አመልክተዋል።
እነዚህ ግለሰቦች ወደ ሀገር ቤት መጥተው ለውጡን ሲመለከቱ በመጸጸት እውነታውን ቢመሰክሩም፣ ሲመለሱ ግን ለጥቅም ሲሉ ዳግም ወደ ቀድሞ አፍራሽ አቋማቸው እንደሚመለሱ አብራርተዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሀቀኛ ጥያቄ ኖሯቸው በበቂ ሁኔታ ምላሽ ያላገኙ እና ስጋት የገባቸው ዜጎች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ በዚህ በኩል የመንግሥትም ክፍተት ሊኖር እንደሚችል አልሸሸጉም።
ሀቀኛ ጥያቄ ያላቸው አካላት በቀጣይ መከተል ስላለባቸው አቅጣጫ ባስተላለፉት መልዕክትም፣ መፍትሔው ተቀራርቦ አብሮ በመሥራት ውስጥ የሚገኝ መሆኑን አመላክተዋል።
ለውጥን ከዳር ቆሞ በመተቸት ብቻ ማሳካት እንደማይቻል የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ "ወንዝን ለመሻገር አብሮ መዋኘት እንጂ ዝም ብሎ ውኃውን መውቀስ አይበጅም" በማለት ሁሉም አብሮ በመዋኘት ለሀገር ግንባታ የድርሻውን እንዲያበረክት መልዕክት አስተላልፈዋል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: