Search

በመንገድ መሰረተ ልማት ዘርፍ የታየው ውጤታማ ሥራ የአዲስ አበባን ተወዳዳሪነት በጠንካራ መሰረት ላይ ገንብቷል

ቅዳሜ ሐምሌ 25, 2018 69

አዲስ አበባ ባለፉት አምስት ዓመታት በከተማ ግንባታ ታሪኳ አዲስ ምዕራፍ ማየቷን የከተማዋ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

አዲስ አበባ ባለፉት አምስት ዓመታት የከተማዋን ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ የቀየሩና ሁለንተናዊ እድገት ያረጋገጡ ዓበይት ተግባራትን አስመዝግባለች።

በመሆኑም አመርቂ ውጤት ከተመዘገበባቸው እና የከተማዋን ዘመናዊነት ካረጋገጡ ዋና ዋና ዘርፎች አንዱ በመንገድ መሰረተ ልማት የታየው አፈጻጸም ነው።

በእነዚህ ዓመታት የተከናወኑት የመሰረተ ልማት ግንባታዎችና የማስፋፊያ ስራዎች የትራፊክ ፍሰቱን ለማቃለል እና የህዝቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

በዘርፉ ከተከናወኑት ዓበይት ተግባራት መካከል አዳዲስ የአስፓልት መንገዶች ግንባታ፣ የነባር መንገዶች ጥገና እና የጠጠር መንገዶች ዝርጋታ ተጠቃሾች ናቸው።

ከዚህም በተጨማሪ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን የሚያገናኙ የኮብልስቶን ንጣፎች፣ ለእግረኞች ደህንነት የተገነቡ የእግረኛ መንገዶች፣ የሳይክል መንገዶች እንዲሁም የህዝብ ትራንስፖርትን የሚያፋጥኑ የፈጣን አውቶቡስ (BRT) መስመሮች ተዘርግተዋል።

የመንገዶችን ዘላቂነት ለማረጋገጥና የጎርፍ አደጋን ለመከላከል የተገነቡት የድረኔጅ (የውሃ መውረጃ) መስመሮች እና የድጋፍ ግንቦችም የዚሁ አጠቃላይ የልማት እንቅስቃሴ አካል ናቸው።

በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በሁለት ምዕራፎች ተከፍለው የተተገበሩት የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች የከተማዋን ገጽታ ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግረውታል።

እነዚህ ፕሮጀክቶች የመንገድ ዝርጋታን ከአካባቢ ውበት፣ ከአረንጓዴ ልማት እና ከመንገድ መብራቶች ጋር በማቀናጀት የከተማዋን የኑሮ ምቹነት በከፍተኛ ደረጃ አሻሽለዋል።

በአጠቃላይ በመንገድ መሰረተ ልማት ዘርፍ የተመዘገቡት እነዚህ ውጤቶች የአዲስ አበባን አህጉራዊ ተወዳዳሪነት በመጨመር ከተማዋ የአፍሪካ መዲናነቷን በጠንካራ መሰረት ላይ እንድትገነባ አስችለዋታል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: