Search

ታሪክ የሚሠራው ዘመቻ፤ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ሀገራዊ ጥሪ

ቅዳሜ ሐምሌ 25, 2018 75

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የጀመረችውን የተፈጥሮ ሚዛንን የማንሰራራትና የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም ሀገራዊ ጉዞን ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገረች ትገኛለች።

በዚህም ባለፉት 7 ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ከፍተኛውን ስኬት አስመዝግባለች።

በዘንድሮ ዓመት ደግሞ 8 ቢሊዮች ችግኞችን ለመትከል አቅዳ በተያዘው ዕቅድ መሠረት እየሠራች መሆኗ ይታወቃል።

ለዚህም በአንድ ጀምበር ብቻ 800 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል አዲስ የዓለም አቀፍ ታሪክ ለመጻፍ ለመላው ኢትጵዮያውያን ጥሪ በማስተላለፍ ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ትገኛች።

የዓለም አቀፉ የአየር ንብረት መዛባት በግብርና እና በአካባቢ ጥበቃ ላይ የደቀነው ስጋት በግልጽ በሚታይበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ የወሰደችው ንቁ የመፍትሔ እርምጃ ለአካባቢው ሀገራት ብቻ ሳይሆን፣ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ትልቅ ማሳያ ሆኗል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ የደን ሽፋን በመጨመር፣ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል እና የውሃ አካላትን በመንከባከብ በኩል ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገብ ጀምረዋል።

የዘንድሮው የ800 ሚሊየን ችግኞች በአንድ ጀምበር የመትከል ዕቅድ ደግሞ ሀገራዊ ቁርጠኝነትን፣ የሕዝብ ትብብርን እና የሎጂስቲክስ ብቃትን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳይ ታላቅ ክስተት ነው።

ይህም ከሀገር ሽማግሌዎች እስከ ወጣቶች፣ ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እስከ ግል ተቋማት ድረስ የሚገኘው መላው የኅብረተሰብ ክፍል በአንድ ዓላማ ሥር እንዲሰለፍ ያደርጋል።

የሚተከሉት ችግኞች ለአፈርና ውኃ ጥበቃ ብቻ ሳይሆን ለአቮካዶ፣ ማንጎ፣ ቡና እና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያላቸው የዛፍ ዓይነቶች ላይ ያተኮሩ በመሆናቸው ለምግብ ዋስትና ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ያበርክታሉ።

ይህንን ታላቅ ዕቅድ ስኬታማ ለማድረግ ችግኞችን ወደ ተዘጋጁት የመትከያ ቦታዎች በወቅቱ ማጓጓዝ የሚያስችል ቅድመ-ዝግጅትና ሎጂስቲክስ ማዘጋጀት እና ኅብረተሰቡ የት፣ መቼና እንዴት እንደሚሳተፍ ግልጽ መረጃ በማቅረብ የተሳለጠ መረጃ ማሰራጨት ያስፈልጋል።

እንዲሁም ጉድጓዶች አስቀድመው መቆፈራቸው በአንድ ጀምበር የሚደረገውን የችግኝ ተከላ የሚያፋጥን በመሆኑ የመሬት ዝግጅት ማድረግ እና የድህረ-ተከላ እንክብካቤ በማድረግ ችግኞቹን መትከል ብቻ ሳይሆን የመከታተልና የመንከባከብ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊና መሠረታዊ ጉዳይ ነው።

ይህ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ዕቅድ የቁጥር ውድድር ሳይሆን፣ ለነገዋ ኢትዮጵያ የሚጣል የተፈጥሮ መሠረት ነው።

የእያንዳንዱ ዜጋ አንድ ችግኝ መትከልና መንከባከብ፣ የሀገራችንን የደን ሽፋን ወደ ላቀ ደረጃ ከማሸጋገሩም በላይ ለወደፊቱ ትውልድ አረንጓዴ እና ምቹ አካባቢን የመተው ሀገራዊ ኃላፊነት ማረጋገጫ ነው። ሁላችንም አረንጓዴ ዐሻራችንን በማስቀመጥ የዚህ ታሪካዊ ክስተት አካል እንሁን።

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: