Search

ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያን አንድነት እና ክብር የሚያጸና ነው - የሃይማኖት ተቋማት አባቶች

ቅዳሜ ሐምሌ 25, 2018 61

በስምንት አበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት እየተመካከረ የሚገኘው ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የኢትዮጵያን አንድነት እና ክብር የሚያጸና መሆኑን በጉባኤው ላይ በመሳተፍ ላይ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶች እና ተመካካሪዎች ገለጹ።

ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በመካሄድ ላይ በሚገኘው በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ላይ፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች ተገኝተዋል።

በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የተለያዩ የእምነት ተቋማት አባቶችና ተመካካሪዎች የምክክር ሂደቱ አሳታፊ፣ አካታችና ነፃ ሆኖ መካሄዱ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ሀገራዊ መግባባትና ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ተስፋ ሰጪ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን ገልፀዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል መልዓከ ሕይወት አባ ወልደ ዮሐንስ ሰይፉ  ሂደቱ አንዱ የሌላውን ሐሳብ ሳይነቅፍ ፍጹም መከባበርና መተሳሰብ በሰፈነበት ሁኔታ እየተካሄደ በመሆኑ እርስ በእርስ ይበልጥ ለመተዋወቅ ማስቻሉን ተናግረዋል።

ይህም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ፍቅር፣ ሰላምና ልማት የሚፈልግ መሆኑን ከመገንዘብ ባለፈ ሰላሟ የተጠበቀ አረንጓዴና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ወሳኝ ምዕራፍ እንደሆነ አመልክተዋል።

ሌላኛው ተመካካሪ አብዱልመጂድ ጃፋር የምክክር ሂደቱ በአካታችነቱና አሳታፊነቱ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው፣ "ይዘን የመጣነው የሀገር ኃላፊነት  በመሆኑ ስለ ሀገራችን ሰላም፣ ልማትና እድገት ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ ምክክር እያደረግን እንገኛለን" ብለዋል።

በሀገራችን የጋራ መግባባት ከተፈጠረ ሌላ የሚጎድል ነገር አለመኖሩን የጠቆሙት ተመካካሪው፣ ሐሳባቸውን በነጻነት መግለጻቸውን በማንሳት ከዚህ ምክክር በኋላ ኢትዮጵያ ትኩረቷን በልማት ላይ ብቻ እንድታደርግ ትልቅ እድል የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል።

በተመሳሳይ ተመካካሪዎቹ ጻዲቁ አብዶ እና አባ አማኑኤል ዮሴፍ በበኩላቸው፣ ለአንድ ሀገር ዘላቂ መረጋጋትና ለጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ መሠረት በሚሆኑ ዐበይት ጉዳዮች ላይ በሠለጠነ፣ በነጻነትና ፍጹም ቤተሰባዊ በሆነ የመደማመጥ መንገድ ሐሳብ እየተለዋወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አክለውም ሂደቱ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ባህልን የሚያጎለብት፣ ለትውልድ የሚሻገር፣ ሰላምን የሚገነባና ኢትዮጵያን ወደ ፊት የሚያሻግሩ ሐሳቦች የሚንሸራሸሩበት መሆኑን ማመልከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: