በሶማሌ ክልል በከፍተኛ ሙቀት፣ በድርቅ እና በበረሃማነት ስጋት ብቻ ትታወቅ የነበረችው የጎዴ ከተማ፤ ዛሬ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አማካኝነት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እየጻፈች ትገኛለች።
የከተማዋን መልክ በግልጽ የቀየረው እና የዋቢ ሸበሌ ወንዝን በወጉ በመጠቀም የለማው የጎዴ ፓርክ፤ የበረሃማነትን ስጋት ወደ ለምለም አረንጓዴነት መለወጥ እንደሚቻል በተግባር ያሳየ አርአያነት ያለው ስራ ሆኗል።
ቀደም ሲል ደረቅ፣ ባዶ እና አቧራማ የነበረው መሬት ዛሬ በማራኪ አረንጓዴ ተክሎችና ዛፎች ተሸፍኗል። ቀደም ሲል ተቀምጦ ዘና ለማለት እና ነፋሻማ አየር ለመውሰድ ይቅርና በአካባቢው ለማለፍ እንኳን አዳጋች በነበሩ ስፍራዎች ላይ፣ ዛሬ የአካባቢው ማህበረሰብ፣ ህፃናት እና አዛውንቶች ተሰብስበው ሲዝናኑ እና ሲቦርቁ መመልከት የተለመደ ሆኗል።
ከጎዴ ፓርክ በተጨማሪ በመሀል ከተማ በሚገኘው አረንጓዴ መናፈሻ ውስጥ ነዋሪዎች ተሰብስበው ሀባብ እየተመገቡ እና ሻይ እየጠጡ ማህበረሰባዊ መስተጋብርን እየፈጠሩ ይገኛሉ።
"እነዚህ መናፈሻዎች በግልም ሆነ በቡድን ለመዝናናት ሳቢ እና ተፊላጊ ስፍራዎቻችን ሆነዋል፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት የተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ተግባራት የከተማችንን ገፅታ ሙሉ በሙሉ ቀይረውታል"የሚሉት ኢስማኤል ሀሰን እና መሀመድ ጉሌይድ የጎዴ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው፡፡
የከተማዋ ስራ አስኪያጅ አቶ መሀመድ ነገይ እንደገለጹት፤ በከተማዋ በፓርኮች እና መናፈሻዎች የተተከሉ ችግኞች የበረሃማነትን ስጋት ከመቀነስና የአየር ንብረትን ከመቀየር ባለፈ፣ ለበርካታ የአካባቢው ወጣቶች አዲስ የስራ ዕድል ፈጥረዋል።
እስካሁን የተገኘውን አበረታች ውጤት እና የህብረተሰቡን ቀና ምላሽ ተከትሎ፣ ፓርኮቹን የበለጠ ለማስፋፋት እና አካባቢውን ከበረሃማነት ስጋት ሙሉ በሙሉ ለማላቀቅ ተጨማሪ የመሬት ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ባለፉት የአረንጎዴ አሻራ ዓመታት የተተከሉ ችግኞች ዛሬ ላይ አድገው ለገሚሱ ጉርስ፣ ለገሚሱ ጥላ ከመሆን ባሻገር፤ ለአየር ንብረት መቃናት እና ለፍጥረታት ህይወት መቀጠል ትልቅ "እስትንፋስ" በመሆን አካባቢን እያደሱ ይገኛሉ።
በቴዎድሮስ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: