Search

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የሌሎች ሀገራት ዲፕሎማቶች በንቃት እየተሳተፉበት ያለ ትልቅ ንቅናቄ ነው - ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

ቅዳሜ ሐምሌ 25, 2018 63

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች ከውጭ ሀገራት ዲፕሎማቶች ጋር በመሆን በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አካሂደዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጥቅም ያላቸው እንደ አቮካዶ፣ ዘይቱን፣ ሮማን እና ብርቱካን ያሉ የፍራፍሬ ችግኞች ተተክለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ የሚካሄደው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የሌሎች ሀገራት ዲፕሎማቶችም በንቃት እየተሳተፉበት ያለ ትልቅ ንቅናቄ ነው ብለዋል።

በዛሬው ዕለት በቢሾፍቱ የተተከሉት የፍራፍሬ ችግኞች ኢትዮጵያ በቀጣይ ለምታስተናግደው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ ማሳያ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በኢትዮጵያ የደን መጨፍጨፍን እና የመሬት መሸርሸርን ለመግታት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ሀገራዊ ንቅናቄ ሲሆን፣ ችግኞችን ለጎረቤት ሀገራት በማከፋፈል ቀጣናዊ የአየር ንብረት ትስስር መፍጠር ተጀምሯል።

መርሐ ግብሩ ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ባሻገር በኅብረተሰቡ ዘንድ አካባቢን የመንከባከብ ባህል እንዲዳብር አድርጓል።

ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ እየተተገበረ የሚገኘው ይህ መርሐ ግብር፣ በሀገራችን ተፈጥሯዊ አካባቢን በመንከባከብ፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ እና አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባት በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

በዋለልኝ ታምር

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: