በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ሲሰለጥኑ የቆዩና ከ28 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፓርኮች የተወጣጡ የፓርክ ጠባቂ ሬንጀሮች በዛሬው ዕለት የምረቃ ሥነ-ሥርዓታቸውን አከናውነዋል።
ተመራቂ አባላቱ በስልጠና ቆይታቸው በፓርኮች ውስጥ የሚኖሩ የዱር እንስሳትን እና የተፈጥሮ ሀብቶችን በብቃት ለመጠበቅ የሚያስችላቸውን ሁለገብ አቅም መገንባታቸው በምረቃው ላይ ተገልጿል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አይሻ ያህያ፣ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብቶች መጠበቅ የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸው፣ ከሬንጀሮች ጋር ተባብሮ በመስራት ሀብታችንን ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ትልቅ አደራ አለብን ብለዋል።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ኮሚሽነር ጎሳዬ ከበደ በበኩላቸው፣ ኮሌጁ የደንና ዱር እንስሳትን የጥበቃ ሥራ ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ እንዲሁም የቱሪዝም ስፍራዎችን ጠብቆ ለማቆየት በጀግንነት የሚሰሩ ብቁ የሬንጀር አባላትን ማስመረቁን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራም፣ ተመራቂ አባላቱ የዱር እንስሳትን ጠብቀው ለሀገር ኢኮኖሚ እና ለቱሪዝም ዕድገት እንዲውሉ ለማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው አስገንዝበዋል።
ተመራቂዎቹ ባገኙት የላቀ እውቀት የተፈጥሮ ፓርኮችን እና የዱር እንስሳትን ለመጠበቅ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ቃል ሲገቡ፣ በዚሁ መርሃ-ግብር ላይ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው የሆነው የሬንጀር ሰራተኞች መዝሙር በይፋ ተዋውቋል።
በአሊ ደደፎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: