Search

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ ዘመቻ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሠርተዋል

እሑድ ሐምሌ 26, 2018 73

ነገ (ሐምሌ 27 ቀን 2018 .) ኢትዮጵያውያን በነቂስ የሚሳተፉበት አረንጓዴ ተስፋን የሰነቀ የልማት ቀጠሮ ተይዟል።

8 ዓመቱን የያዘው የኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማት ባለፉት ዓመታት 48 ቢሊዮን ችግኞችን ከመሬት አገናኝቶ ለመላው ኢትዮጵያውያን ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶችን አበርክቷል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ ምርት እና ምርታማነትን ያሻሻለ ሲሆን ወንዞችን ከደለል በመታደግ የኃይል ማመንጫዎቻችንን ደኅንነት አስጠብቋል እንዲሁም በረሃማነትን በመቀነስ ተስማሚ የአየር ንብረትን ለግሷል።

ከሁሉም በላይ ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ዘይቱን እና መሠል የፍራፍሬ ዓይነቶች ለምግብነት የደረሱ በመሆኑ የምግብ ዋስትናችንን ማሻሻል ችለዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ችግኝ ጣቢያዎች ሲገኙ ለበርካቶች የሥራ ዕድል ፈጥረው ችግኞችን በማፍላት እና ለገበያ በማቅረብ ዘርፉ ለዜጎች ሁነኛ የገቢ ምንጭ ሆኗል።

ተስፋን እንትከል በሚል መሪ ሐሳብ በነገው ዕለት 800 ሚሊዮን ችግኞች በሚተባበሩት የኢትዮጵያውያን እጆች በአንድ ጀምበር ዘመቻ ይተከላሉ።

ለዚሁ ዘመቻ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ ነው፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ከሊፋ እንደገለጹት በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች የጉድጓድ ዝግጅት እና ችግኞችን ወደ መትከያ ቦታዎች የማጓጓዝ ሥራ እየተሠራ ነው።

በዕለቱ የክልሉ ማኅበረሰብ በማለዳ በመውጣት በዚህ ሀገራዊ መርሐ ግብር በንቃት ይሳተፋል።

በጀማል አሕመድ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: